ከአጋሬ ጋር አስራ ሶስት አመት ነው የምንተዋወቀው በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከሆንን ደግሞ አስረኛ አመታችንን ለማክበር ወራቶች ይቀሩናል።ለእኔ ደስተኛ ትዳር ነው። ገሃድ ቢወጣ እና ማሳወቅ ብችል ደስ ይለኝ ነበር። እንደዛም ባይሆን እንኳን በራሴ ቤት ውስጥ፣ በራሴ ስፍራ ላይ ይሄን ደስታ ማጣጣም በመቻሌ ራሱ አመስጋኝ ነኝ።
አስተዳደጌ እርጋታ ያልነበረበት ነበር፡፡ አባቴ በጣም ጠጪ ነበር፤ ታናሽ ወንድም እና እህት አሉኝ፡፡ ያደግንበት ቤት ለረዥም ጊዜ ሰላም ያልነበረበት ቢሆንም እኔ በተለየ መልኩ ከወንድሜም ሆነ ከእህቴ በተለየ መልኩ ለአባቴ ቅርብ ነበርኩ (መጠጥ ሳይጠጣ ሲቀር)፡፡ ትዝ ይለኛል ታላቅ ወንድሜ ፈሪ ቢሆንም ወንድነቱ እየያዘው ከሰው ይጣላ ነበር፤ ብዙ ጊዜ ተደብድቦ ስለሚመጣ አባቴ ለእሱ ብዬ እንድባደብ ይልከኝ ነበር፤ ሄጄ ተፈናክቼ እመጣ ነበር ከልጅነቴ ጀምሮ ወንዳወንድ ነበርኩ፤ ለዛም አባቴ ‹‹ሂድና ተደባደብ ›› ይለኝነበር፡፡ አሁን ቢያስቀኝም አሪፉም ትውስታዬ ነው። የምደባደባቸው ልጆች አራት አምስት አመት ታላላቆቼ ነበሩ። ፍርሃት የሚባል አልነበረብኝም፤ ተደባድቤ ስመለስ በጣም ደስ እያለኝ በኩራት ነበር የምመለሰው፡፡
እናቴ ደስ ባይላትም ኳስም ከወንዶች ጋራ እጫወት ነበር፡፡ እሷ ቤት ውስጥ ስራ እንዳግዛት ብትፈልግም እኔ ግን እርግጫው ስለሚበልጥብኝ ጫወታው ላይ አዘወትር ነበር፡፡ እናት ሳለች ሩጥ እንደሚባለው እስከ አስር አመቴ ድረስ እንደዛ ነበር የቀጠልኩት። እናቴ ስታርፍ ግን ሁሉም ነገር ተቀያየረ እና ከእህቴ ጋር አያቶቼ ጋር አዲስ አበባ መጣን፡፡ አያቴ ጋር ከኛ ውጪ ሁለት ሴት የአጎትና የአክስት ሴት ልጆች ነበሩ፡፡እድላችን ሆኖ የአያቴም ቤት ከእኛ ቤት የተለየ አልበረም፤ ከባለቤቷ ጋር እስክትፋታ ድረስ በመሃከላቸው ከፍተኛ ፀብ ነበር፡፡
አያቴም ጋር ከመጣሁ በኋላ እንዲሁም አድጌ ጊቢ ከገባሁም በኋላ ኳስ መጫወቴን አላቆምኩም ነበር። የአያቴ ቤት የተለያየ ዘመድ የተሰበሰበበት ስለሆነ መናገር ከምችለው በላይ ብዙ ብጥብጦች እና ፀብ የበዛበት ቤት ነበር፡፡ በመጨረሻም አያቴ ከባሏ ጋር ተፋታችና ከመቼውም በበለጠ ቅርብ ሆነን ነበር፤ በርግጥ አሁንም ቅርበት አለን ግን እኔ ከእህቶቼ በበለጠ ከእሷም ጋር ሆነ ከእህቶቼ ጋር ርቀት ፈጥሬያለሁ። በጣም ሰፊ ቤተሰብ ብንሆንም ግላዊ ህይወት ላይ ሁሉም ልወስን የሚል አይነት ቤተሰብ ነበር። ቀረቤታው እንዳለ ሁለሀ ቁጥጥሩም በዛው ልክ ነበር። የእኔን የግል ህይወት በተሻለ መንገድ ደብቄዋለው ብዬ አስባለሁ።
በዚህ አይነት ውጥረት በሞላበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ የራሱ የሆን ችግር ቢፈጥርም የምወቅሰው አካል የለኝም። ልጅ ሆኜም አሁንም አባቴን በጣም ነው የምወደው፡፡ አያቶቼ የእናቴ ቤተሰቦች ስለሆኑ እዚህ እነሱ ጋር ስለሱ የሚወራውነገር መጥፎ ነው፡፡ ውሸት ሆኖ ባይሆንም ስለእሱ የሚናገሩት እውነታ ግን አስፈሪ ነበር። ከዚህ የተነሳ አንዳንዴ እንዴት እንደዚህ አይነት ሰው መውደድ እችላለሁ ብዬ ከራሴ ጋር እታገል ነበር፡፡ እሱን መውደድ ከቻልኩ እኔ ራሴ ምን አይነት ሰው ነኝ? እያልኩ እጨነቅ ነበር። ከዛ በተጨማሪ ምንም እንኳን እህቴ በሳል ብትሆንም የሚፈጠሩትን ነገሮች እንዳታይ እሷን የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረብኝ፡፡ ነገሮችን ቀለል አድርጌ ማየት ይቀለኛል አንዳንድ መጥፎ ክስተቶችን ከአእምሮዬ ሁሉ ሳይቀር ብሎክ ያደረግኳቸው አሉ። ለምሳሌ እናቴ እህቴን እርጉዝ ሆና አባቴ ከደረጃ ላይ ገፍትሮ ጥሏት ነበር። እንደነዚህ አይነት ትውስታዎችን በተቻለ መጠን ለአለማሰብ እሞክር ነበር። ሌላም ግዜ እናቴን በተደጋጋሚ ይመታት ነበር፤ ያም ለኔ ኖርማል ነበር። ምክንያቱም እኔ ራሴን በጣም አመፀኛ እና መደባደብ የምወድ ሰው ስለነበርኩ ነው። ከፍ እያልኩ ስመጣ እነዚህ ነገሮች ልክ እንዳልሆኑ እየተረዳሁ ስመጣ ከራሴ ጋር ፀብ ውስጥ ገብቼ ነበር። በዚህ ምክንያት አባቴ የሚያደርገውን ነገር በዚህ ምክንያት ነው የሚያደርገው ብሎ በምክንያት ለመረዳት ከባድ ነበር። አባቴ ለእኔ መልካም ሰው ነበር፤ ስለዚህ ከፍ እያልኩም ስመጣ ለእሱ ያለኝ መውደድ በፍፁም ሊቀንስ አልቻለም።
በብዙ ሁከት፣ ረብሻ እና አመፅ ውስጥ ማደግ በከፍተኛ መጠን ተፅዕኖ አሳድሮብኛል። ተሰብስበን ይሁን ወይ ከአጋሬ ጋርም ተቀምጠን አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ ቢያወራ በጣም ነው የምረበሸው፣ ክርክር እንዳልሆነ እያወቅኩም ድምፅ ከፍ ካለ በቃ ውስጤ ምቾች ይነሳል። አሁንም ድረስ መከራከር፣ መጨቃጨቅ እና መጣላት የማይመቸኝ ሰው ነኝ። በዛም ምክንያት ብዙ ጊዜ ራሴን ከንደነዚህ አይነት ቦታዎች በፍጥነት ማግለል ይቀለኛል። ከማንኛውም ሰው ቢሆን ከተረጋጋ በኋላ ማውራቱን እመርጣለው፡፡ ይሄ ሁሉ ልጅነቴ ላይ የነበረው ሁኔታ ተፅዕኖ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ምንም እንኳን ልጅ እያለሁ ከእናቴ ሞት በኋላ የእሷ ዘመዶች ጋር መጥቼ የኖርኩ ቢሆንም ከአባቴ ጋር ቀረቤታ እና መዋደድ እንዳለኝ ሁሉም ያውቁ ነበር፡፡ ሃይስኩል እስክገባ ድረስ አያቶቼ ጋር ልኑር እንጂ ሲመጣ እና ላገኘው ስል የነበረኝን ጉጉት ላለማሳየት ደብቄ አላውቅም ነበር፡፡ ግን አያቴም ከባሏ ጋር በእኛ ምክንያት ከተፋታች በኋላ ትኩረቷ ሙሉ በሙሉ እኛ ላይ ነበርና ከእሱ ጋር ስገናኝ ደስ እንደማይላት መገንዘብ ጀመርኩ። ከዛ የተነሳ ስለ እሱ ክፉ ሲያወሩ ሳልወድ በግዴ ለማስመሰል ያክል ከእነሱ ጋር እየተባበርኩ ክፉ ክፉዉን አወራ ነበር። ከእሱም ጋር ስሆን ስለ እነሱ ክፉ ሲያወራ የፈለገውን እሰጠው ነበር። ሁሉንም ላለማስከፋት ስል ራሴን እየጠላሁም ቢሆን የሆኑትን ለመሆን እሞክር ነበር። አያቴ እኛን ለማሳደግ ስትል ትዳሯን በመተዋም ትልቅ የተጠያቂነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ለአባቴም ሆነ ለእሷ ብዋሻቸው ተገናኝተው የሚያወሩበት መንገድ ስለማይኖር ሁለቱም ከእኔ የፈለጉትን እንዲሰሙ አደርግ ነበር፡፡ በርግጥ አሁንም ድረስ እንደዛው ነው ያለነው። የሆነ በስህተት እንኳን እሱን መክተን ከተናገርን ለወራት ይዘፈንብናል፤ ያንንም ስለምንጠላ ምን ብንናፍቀው ስሜታችንን አውጥተን አንናገርም ነበር። ይህ እኔ እና እህቴ ላይ ሁለት ቦታ መወጠርን የሚፈጥር ውጥረት ነበር፡፡
የኩዊር ጉዞየን ሳስብ የጠነከረ የምለው ነገር ኖሮኝ ባያውቅም እንዲሁ የሴት ክረሾች ነበሩኝ። ቢሆንም ግን ሴቶችን በጣም እሸሽ ነበር፡፡ ካምፓስ ከገባሁ በኋላ እንደውም አንድ የዶርሜ ልጅ ጋ ተቀራረብንና ‹‹ሚስቴ ናት›› እያለች ታወራ ነበር፤ ትዘፍንልኛለች፣ አንድ አልጋ ላይ ነው የምንተኛው። እየቆየ ለእሷም ለየት ያለ ስሜት እየተፈጠረብኝ መጥቶ ነበር።
የዚህ አይነት ነገር ሰምቼም አይቼም አላውቅም ነበር፤ ላውቅበትም የምችልበት መንገድ አልነበረም። እንዲሁም ስለ ፍቅር ግንኙነቶች ሀሳቡም ፍላጎቱም ኖሮኝ አያውቅም ነበር እና ያ ስሜት ለሷ ሲሰማኝ የበለጠ አስጨናቂ ነበር፡፡ የዛ አይነት ነገር ሊሆን እንደሚችል ምንም ማሰብ አልቻልኩም ነበር፤ የሚመስለኝ ‹‹በቃ ይቺን ሴት እንደጏደኛ እወዳታለሁ›› ነበር። ከዛ የዘለለ ነገር ምንም አናደርግም ነበር፡፡ እንደዛ ሆነን ሁለት አመት ከቆየን በኋላ እሷ የወንድ ፍቅረኛ ስትይዝ እኔ ጋር የፈጠረው ስሜት የቅናት ነበር። እሱን ልታገኘው ስትሄድ መበሳጨት እና መቆጣት ስጀምር ነው ቆም ብዬ ራሴን ይህ ኖርማል አይደለም እኔ ፍቅርኛ ብይዝ እሷ እንደዚህ ይሰማታል? እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ ቀስ በቀስም ራሴን ከዛ ስሜት ለማላቀቅ እና ከሷ ለመራቅ ሞከርኩ።
አሁን ያለችውን የፍቅር አጋሬን ከያኔ ጀምሮ ፌስቡክ ላይ አወራት ነበር (2003 አከባቢ) የተለየ ወሬ ባይሆንም እንዲሁ የባጥ የቆጡን ነበር የምናወራው፡፡ በሰአቱ ምንም አይነት እርምጃ ለማድረግ ሞክሬ አላውቅም ነበር፤ ክለብ ወጥተን ብንጨፍር እንኳን ራሴን ከእነሱ ለማሸሽ ነበር የምሞክረው፡፡ በዚህ መሃል ወንዶች ሁሉ ዴት ማድረግ ጀምሬ ነበር።
ሶስተኛ አመት ሆኜ ነው ለመጀመሪያ ግዜ የኤለን ዲጀነረስን ሾው የተመለከትኩት ምናልባት እኔም እንደሷ እሆናለሁ ብዬም ያሰብኩት፡፡ ነገር ግን በሰአቱ ያን ማሰብ በራሱ እንደ ከባድ ስህተት እንደሆነ ነገር ይሰማኝ ነበር። ቤተክርስቲያን ተሳታፊ የነበርኩ ልጅ ነበርኩ፤ የሚሰማኝ ስሜት ልክ እንዳልሆነ በሚሰበከው ሁሉ እሰማ ነበርና ያንን ሀሳብ ከእኔ ለማውጣት ከልክ ባለፈ መልኩ ከወንዶች ጋር ዴት መውጣት ጀመርኩ። እንዲሁ ለሽሽቱ እንጂ ምንም አይነት ስሜት ኖሮኝ አልነበረም። ከወንዶቹ ጋ ያለኝን ግንኙነትም ሁሉም እንዲያውቁት አደርግ ነበር። ሰዎች ወንዶችን በፍቅር እንደማልፈልግ እንዲያውቁ አልፈለግኩም ነበር። የመጀመሪያ ዴት ስወጣ እንኳን ጏደኞቼ ባሉበት እሄድ ነበር፤ እያዩኝ እሳሳም እና እተቃቀፍ ነበር፤ አሁን ሳስበው እስቃለሁ ምክንያቱም በሰአቱ ምንም ነገር ከእነሱ ጋር ማድረግ ፈልጌ አላውቅም ነበር። ሩም እንያዝ ሲሉ እንኳን ‹‹እኔ ከትዳር በፊት ሴክስ አላደርግም›› ስላቸው ቤተክርስቲያን እሄድ ስለነበር “የቸርች ልጅ” ብለው በቀላሉ ይፋቱኝ ነበር። ምክንያቱም እንኳን ሌላ ነገር ቀርቶ ከሳምኳቸው በኋላ ራሱ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ነበር፡፡
አምስት አመት በዛ መንገድ ካሳለፍኩ በኋላ የማልረሳው አንዴ የሴቶች ዶርም ተቃጥሎ ወንዶች ሊረዱን እኛ ጋር መጡ የዛኔ ቦርሳዎችን እና ሻንጣዎችን ከእሳቱ እያሸሹ መንገድ ላይ ይዘረግፉት ነበር እና በጣም ብዙ ዲልዶዎች ከየልብሱ መሀል ይገኙ ነበር። በሰአቱ ምን እንደሆኑም አላውቅም ነበር። ከዛ በኋላ ግን ነገሮች እየገቡኝ መምጣት ጀመሩ። አንዳንድ ነገሮች ማንበብብ ጀመርኩ ራሴን ግን መቀበል እስኪያቅተኝ አወዛገበኝ፣ ተመላልሼ ለራሴ እኔ በሴት አልማረክም እያልኩ ልነግረው እና ላሳምነው እሞክር ነበር። ውዝግብም መፀየፍም ውስጥ ነበርኩ።
እዛው ካምፓስ እያለን ዶርሜ ፕሮክተሯ ቢሮ ጎን ነበር። የዛኔ ከሌሎቹ በእድሜም በሰውነትም አነስ እል ስለነበር ፕሮክተሯ በጣም ትሳሳልኝ እና ትወደኝ ነበር። አንዴ ሻይ ሸተተኝ ብላ ወደዶርማችን ስትመጣ ሁለት ሴቶች ሲሳሳሙ አየችና በድንገጤ መጥታ ለእኔ ነገረችኝ፤ ሁኔታዋ አይረሳኝም ከባድ ድንጋጤና የመፀየፍ ስሜት ነበረው። እኔንም ‹‹እንደነዚህ እንዳትሆኚ አደራ› ብላ አስጠነቀቀችኝ።
ስለተመሳሳይ ፆታ ፍቅር በተደጋጋሚ እሰማ የነበረው ነገር ጥላቻንና በሀይማኖት የተወገዘ እንደነበር ስለሆነ ከዛ የተነሳ የሚጠላ ሰውማ ልሆን አልችልም እያልኩ ትግል ውስጥ እገባ ነበር፡፡
አፓረንት ልንወጣ አመቱን ስንጨርስ ከዶርም ልጆች ጋ ክለብ እንግባ ተባብለን ሄድን፤ እንግዲህ ጊቢ ከገባሁ በኋላ በተወሰነ መልኩ ሴት ጓደኞች ብይዝም ልማረክባቸው ከምችላቸው ጋር ግን አልቀራረብም ነበር። ያኔ ከሁለት ሴት ጓደኞቼ ሆነን እየደንስን የማላውቃት የእዛው ሀገር ልጅ ከመሬት ተነስታ ከንፈሬን ሳመችኝ፤ በሰአቱ ስንቴ ከወንዶች አደርገው የነበረ ነገር ከሴት ጋ ሲሆን ተሰምቶኝ የማያውቅ አይነት ስሜት ነበር የተሰማኝ። መላ አካሌን ውርር አደረገኝ፤ ድንጋጤ ላይ ስለነበርኩ ግን ገፍቻት ተጣልቼ ነበር የወጣሁት።
ከዛ በኋላ ግን ሌት ተቀን የማስበው መሳሳም ነበር። ክለብም እንውጣ ስባል ይሄን አጋጣሚ እያሰብኩ አንዷ ስማኝ መልሼ ብስማትስ በሚል ፍርሀት ወይ ብዙ ግዜ አልወጣም ከወጣሁ ደግሞ ጥጌን ይዤ ርቀቴን ጠብቄ ነበር የምቀመጠው።
አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ አጋሬ ጋ ለመጀመሪያ ግዜ ተገናኘን፤ ከተገናኘን በኋላም አመት ያህል በተከታታይ ስንገናኝ በኔ በኩል ያለውን ስሜት ባውቅም እኔም ልቀበለው አልፈለግኩም አልፌ ተርፌም አያቴንና የምወዳቸውን ሰዎች በሙሉ ማስቀየም አልፈለግኩም። አይናቸውንስ እንዴት አይቼ እነግራቸዋለሁ ብዬ ስለፈራሁ ምንም ሳይፈጠር ቆየን።
ያኔ አውራ ጣቴ ላይ የማደርገው የቆየ ቀለበት ነበር እና አንድ ቀን ታክሲ ውስጥ ሆኜ አንዲት ሴትዮ ‹‹እናቱ ይሄ እኮ የሌዝቢያኖች ቀለበት ነው፤ አውራጣታቸውም ላይ የሚያደርጉት እነሱ ናቸው›› ብላ አስደነገጠችኝ። በስመአብ አልኩና ሌሎች ጣቶቼ ላይ ስለማይበቃኝ እንደሆነ ነግሬ መሃል ጣቴ ላይ አደረግኩት፡፡ ያንለት ቢሮ እንደገባሁ ጉግል ማድረግ ጀመርኩ፤ ከዛ በርካታ ቪዲዮዎችን ማየት ጀመርኩ፤ ያኔ ነው በትክክል ሴቶችን እንደምወድ የተገለጠልኝ፤ መቀበል ግነእ አልፈለግኩም።
የዚህ አይነት የድብቅ ህይወት በጭራሽ መኖር አልፈለግኩም ነበር፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን ለአሁኗ አጋሬ ሁሉንም ግልፅ አድርጌ ነገርኳት። ስለራሴ የማውቀውንም ስለእሷ የሚሰማኝንም። ከእሷ ጋር የተዋወቅነው በዜጋ አካውንት አልነበረም፤ የዜጋ አካውንት አሁንም የለኝም። ኦንላይን የዘፈን አካውንት ነበርና እዛ ውስጥ ተመሳሳይ አርቲስቶች በመውደዳችን ምክንያት ፌስቡክ ሰጀስት አድርጎኝ ነበር የተዋወቅነው። ጊቢ ሆኜ አራት አምስት አመት በኢንተርኔት ብቻ አውርተናል። አዲስአበባ ከተመለስኩም በኋላ አንድ አመት ያህል ሳንገናኝ እንዲሁ የጏደኛ ወሬ አውርተን ነበር።
አንዳንዱን ግን መለስ ብዬ ሳየው የተወሰነ ፍለርት ማድረግ ነበረው። ዶርም ዋይፋይ ስላልነበር እሷን ለማውራት ስል በጨለማ ዛፍ ስር በጅብ ጩኸት ታጅቤ ነበር ከሷ ጋር የምፃፃፈው፤ ሰው እያጠና ሲያመሽ እኔ ከእሷ ጋር ወሬዬን እቀድ ነበር። በየቀኑ ከማውራታችን የተነሳ ካላወራኋት የመደበር ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ለእሷ የነበረኝን ስሜት የምረዳበት መንገድ አልነበረም፤ በዙሪያችንም ብዙ ዜጋ አልነበረም። ከዛ ሁለየ በኋላ ነው አዲስአበባ መጥቼ አንድ አመት ከአለፈኝ በኋላ እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ የሚሰማኝን የነገርኳት፤ ደስ የሚለው እሷም እንደዛው እንደሚሰማት ስትነግረኝ ነው። ወዲያው ዴት ማድረግ ጀመረን፤ ዘጠኝ አመት በዛ ሁኔታ ከቆየን በኋላ ነው የዜጋ ኮሚዩኒቲ ሁሉ እንዳለ ያወቅነው፡፡
በመጀመሪያ ብቻችንን እንዳልሆንን ሲሰማኝ የነበረኝ እረፍት ቀላል አልነበረም። እኛ ላይ ብቻ ያለ ወይም ጭንቅላቴ ላይ ያለ ችግር አይደለም የሚል ሰላም ሰጠኝ። ሌላው እኔና አጋሬ ችግር ቢገጥመን ወይ እንደሰው ብንጣላ ልናወራው የምንችለው አካል አልነበረም እና ከእሷ ተጣልቼ ደበረኝ ብል የሚረዳኝ ሰው አለመኖሩ እንኳን ያብከነክነኝ ነበር። ምንም እንኳን ግላዊ ነገር ጠልቄ ለሰው ማውራት ባልፈልግም፤ አንዳንዴ ከበድ ያለ ፀብ ካጋጠመ “እንዲህ እኮ ተፈጠረ” ብየ ልነግረው የምችለው ሰው መኖሩን ማሰቡ በራሱ እረፍት አለው። ሊረዱ፣ ሊያግዙ የሚችሉ ሰዎች ኮሚዩኒቲዉ ውስጥ መኖሩ ደስ ይላል። እኔና እሷ ዘጠኝ አመት እንደጥንድ ስንኖር ይሄን አናውቅም እና ቀላል አልነበረም። እኔ እንዳልኩት መጨቃጨቅ አልወድም፣ ፀብ ሲፈጠርም እሸሻለሁ ወይ በውስጤ ነው አፍኜው የምቀመጠው እና ከአቅሜ በላይ የሆነ ግዜ የማይሆን ነገር ነው የምፈጥረው። ሰው ቢኖር ግን ማማከሩ አለ፣ መወያየቱ አለ። ለፀብ ብቻም አይደለም የሆነ ነገር ላደርግላት ሳስብ እንዲያማክረኝ የምጠይቀው ሰው ማግኘት ማለት በራሱ በቃላት የሚገለፅ አይደለም።
ሰው ሲኖር ማህበራዊ ህይወት ይኖራል፣ የሚሰማኝን እንዲሰማኝ መፍቀድ እችላለሁ። ኮሚዩኒቲ ማግኘት የሚታመን አልነበረም፤ እጅግ ድንቅ ነበር።
ይህን ግንኙነት ስጀመር ብዙ ሰዎችን ሸሽቻለሁ አጋሬ እንድትታወቅ ስላልፈለግኩ ራቅኩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሌዝቢያን ጥንዶች ቤት ሄደን ዊርድ ነበር የሆንነው። እነሱ ኮሚዩኒቲው ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተዋል እና ከእኛ የተሻለ ግንዛቤ ስለነበራቸው ነፃ ነበሩ፤ እኔ እና እሷ ግን እዛ የተገናኘ ሰው ነበር የምንመስለው። አይኗን እንኳን መመልከት አልቻልኩም ነበር፤ ምክንያቱም የተቃራኒ ጾታ አፍቃሪ ጓደኞቻችንን ስናገኝ፤ በተለይ ከእሷ እህት ጋር በጣም ቅርብ ነበርንና ፍቅራችን እንዳይታወቅ ርቀታችንን በመጠበቅ ስሜታችንን የገዛን ሰው ነበርን።
የቅርብ ጓደኞች ሁሉ አንመስልም አይደለም ፍቅረኞች፣ ያም ስለለመደብን ነው መሰለኝ ከካፕሎቹም ጋር ሆነን
የቅርብ ጓደኞች ሁሉ አንመስልም አይደለም ፍቅረኞች፣ ያም ስለለመደብን ነው መሰለኝ ከካፕሎቹም ጋር ሆነን እንደዛ ነበር የሆንነው፡፡ ወጥተን ስንሄድ ራሱ “ዊርድ ሆንን እንዴ?” እየተባባልን ነበር። እየቆየ ግን በደንብ ኮሚዩኒቲውን መቀላቀል አለ፣ ጥሩ ሰዎች መተዋወቅ አለ፣ ቀስ በቀስ ማህበራዊ ህይወት መመስረት ውስጥ እና ምቾት ማግኘት ውስጥ ተገባ።
አጋሬ በጣም ቁጥብና ቤተኛ ስለሆነች ከእነሱ ጋር ሆኜ ብዙ ሰዎች ተዋወቅኩ፤ አንዳንድ ቤቶች መሄድ ጀመርኩ። ያኔ ገና ነበር በቃ “ጌይ ነን”ብለን ለማንነታችን ራሱ ስም የሰጠነው፡፡ አብረን መሆናችን እና ደስተኛ ከመሆናችን በቀር ስም አልሰጠነውም ወይም እንዲህ ነን አላልንም ነበር።
እየቆየሁ ነፃነት በደንብ ሲሰማኝ ለአንዲት ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪ ጓደኛዬ ዜጋነቴን እና አጋር እንዳለኝ እንዲሁም እንደተጫጨን ነገርኳት ‹‹ድንግል ነሽ እንጂ ሌዜቢያን አይደለሽም ዲክ ሞከር አለብሽ›› ብላ አለችኝ። ራሴን የተሻለ ስለማውቅ ብዙም ቅር አላሰኘኝም ነበር። በዛ ሰአት የራሴ ኮሚዩኒቲ እንዳለኝ አውቄ ነበርና የሚያውቀኝ እና የምወዳቸው አውቀው ቢተዉኝ እንኳን ሌሎች ሰዎች አሉኝ፣ የሚል ድፍረት እና መተማመን ሰጥቶኝ ነበር። የምወደውን የሚወዱ፣ የሚረዱኝ ሰዎች አይጠፉም ብዬ መቀበል ጀመርኩ፡፡
አጋሬን ዴት ማድረግ ከጀመርኩ በኋላ ሌሎች የምሄድባቸው ቦታዎች ነበሩና ከእሷ ጋር ብዙም አንታይም ነበር፣ ራት ለመብላት እና ሻይቡና ለማለት ካልሆነ በቀር ብዙ አብረን አንታይም፣ ስንሄድም በተለያየ ግዜ የተለያየ ቦታ ነበር የምንሄደው።
ለብቻዬ ስሆን ደግሞ ጓደኞቼን በተደጋጋሚ የማገኝባቸው ቦታዎች ላይ እሄድ ነበርና እንዴት እንደሆነ ሳላውቅ ‹‹ ሌዝቢያን ናት›› ተብሎ መወራት ተጀመረ። በውስጤ እንኳንም አወቃችሁት እያልኩ፤ በአፌ ግን ሙሉ ለሙሉ ካድኳቸው። “ከወንድ ጋር ካልታየሁ ሌዝቢያን ነኝ ማለት ነው?” ብዬ ተናደድኩባቸው፡፡ አምነው ቢቀበሉኝም ግን የተወሰነ ፍርሃት ስለተሰማኝ ከእነሱ ጠፋሁ። በጊዜ ብዛት የነበሩኝ ግሩፖች፣ ጓደኞች እየጠበቡ መጡ፡፡
እንደ እናቴ የማያት አክስት ነበረችኝ እና ገና ቤት የለቀኩበት ጊዜ ላይ ስራ ልሄድ ተዘጋጅቼ ለባብሼ ስወጣ አለባበሴን አይታ “እነዛን ሌዝቢያን ነው የምትመስይው” አለችኝ። እኔም “እንዴት?” ስል አጎቴ “ያላሰበችውን አታሳስቢያት” ብሎ ተቆጣት። ከዛ በኋላ ግን የተወሰነ አለባበሴን የበለጠ እንደ ሴት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ አባቴ ከልጅነቴ ጀምሮ የሚጠራኝ አንተ እያለ ነበር፣ “ በላይ ዘለቀ” ይለኛል እና እሷን ዴት ማድረግ ስጀምር ብዙ ለነገሮች ትኩረት መስጠት ጀመርኩ። ልጅ ሆኜ ስለማላውቅ ምንም አይመስለኝም ነበር፤ ነፍስ አውቄ ፍቅር ስጀመር ግን በአለባበሴ የሚያውቁኝ ከሆነማ መቀየር አለብኝ ብዬ አሰብኩ። ቀለበት ሲሉ ቀለበቴን ቦታ መቀየር፣ ልብስ ሲሉ ልብስ መቀየር፣ አኳኋን ሲሉ አኳኋኔን ስቀይር ቆየሁ። አረማመዴንን መቆጣጠር ጀመርኩ፣ እጄን ከኪሴ ማውጣት፣ አቀማመጤን ሁሉ ሳይቀር መለወጥ ነበረብኝ፡፡ ከቤት ከወጣሁ በኋላ ግን የሆነ ነፃነት ስለተሰማኝ ማንም አያገባውም ከዚህ ወዲያ ማለት ጀመርኩ፡፡
ቤት ለቅቄ የወጣሁበት አንዱ ምክንያት የአግቢ ጥያቄ ነበር። ታላቅ ስለነበርኩ ጭቅጭቁ ለከት አልነበረውም፣ እለት እለት ነበር። በተጨማሪም ስልክ ለማውራት፣ ለመግባት ለመውጣት ነፃነት አልነበረም። ያን ሁሉ ሽሽት ነበር ለቅቄ የወጣሁት።
በእውነቱ ወጣች ተብሎም የሚለቅ አይነት ንዝንዝ አልነበረም፣ አሁንም ድረስ ቤት ስሄድ የሚነሳ ንዝንዝ ነው። የእድሜዬ ነገር ከኔም በላይ ያሳሰባቸው እነሱን ነው። “መቼ ልታገቢ ነው፣ እህቶችሽም ባንቺ ምክንያት ቆመው ቀሩ፤ ታላቅ ሳታገባ እንዴት እነሱ ያገባሉ?” እያሉ ተጠያቂነት እንዲሰማኝ ያደርጉኛል።
ቀሩ፤ ታላቅ ሳታገባ እንዴት እነሱ ያገባሉ?” እያሉ ተጠያቂነት እንዲሰማኝ ያደርጉኛል።
እነሱ በሚገምቱት ተቃራኒ ደግሞ እኔ እዚህጋር የራሴን ትዳር መስርቼ እየኖርኩ ነው። ይሄ ስሜት እና ጫና ደግሞ በጣም ነው የሚረብሸው። የበዛብኝ እለትም “ከዛሬ በኋላ አግቢ ካላችሁኝ አታዩኝም” ሁሉ ብያቸዋለሁ ግን ያን ያህል ጥቅም የለውም።
እህቴ እና ከዝኔ ያላቸው ቀረቤታ በጣም ቅርብ ስለሆነ እኔና ፓርትነሬ ብዬ ሳወራ እንዳያውቁብኝ እፈራ ነበር። በቅርብ እንደውም እህቴ ለምን እንደማላገባ ስትጠይቀኝ ምላሼ የነበረው በቤተሰባችን ውስጥ ብዙ ያልተሳካ ትዳር ያላቸው ስለሚበዙ ለየቱ የተሳካ ትዳር ነው የማገባው የሚለው ነበር። ያኔውኑ ሌላኛዋ እህቴ የፓርትነሬን ስም ጠርታ “እሷን ባል ብላ ይዛ እንዳትመጣ ነው የምፈራው” ብላ አሳቀችን። በዛው ወሬው ትንሽ ተለጠጠና “ማነው ባል፣ ማነው ሚስት ? አንቺ ነሻ እንደ ባል ምትሆኚው?” ሲሉ “ጤነኞች አይደላችሁም እንዴ?” ብዬ አሳስቄ አለፍኩት።
ያው በነዚህ በነዚህ ምቾት በማይሰጡ ወሬዎች ምክንያት ከገዛ ቤተሰብ ጋ መራራቅ ይመጣል። በጣም በቅርቡ ወንድሜ እና አክስቴ ከውጪ ሲመጡ አያቴ ጋር መሄድ ስለነበረብኝ እዛ ትንሽ ቆየሁ፣ እዛ ሆኜ ደግሞ አጋሬን ቤት ብቻዋን ስለተውኳት እሷጋ ደግሞ ትንሽ እየቆየሁ ባላንስ ለማድረግ ብሞክርም፣ ሁሉም ባል ወይ የሚያስቸኩል ልጅ እንደሌለኝ ስለሚያውቁ ቤት ልሂድ ባልኩ ቁጥር “ምን አስቸኮለሽ” እያሉ ይነዘንዙኝ ነበር። አሞኝ ነው ደክሞኝ ነው ማለት እስካፍር ድረስ ስንት ግዜ በዛ እያሳበብኩ ወደሷ እመለስ ነበር።
ከቤተሰብ ጋ በደንብ ቅርርብ ስለነበረን ከአክስት እና አጎቶቼ ጋ እየወጣን እንጠጣ ነበር፤ ከግዜ በኋላ ግን ደግሞ ሰክሬ ባፍረጠርጠውስ እያልኩ በፍርሀት ከነሱ እየተነጠልኩ መቅረት ጀመርኩ።
ከፍቶኝ፣ ደብሮኝ፣ ዛሬ እንዲህ ሆኖ እንዲያ ሆኖ እንዳልል እያልኩ ሲደውሉልኝ ለስራ ከከተማ ውጪ ነኝ እያልኩ፤ ምክንያት መፍጠር ጀመርኩ።
ቤት እንምጣ ሲሉም አስቀድመው ፕሮግራም እንዲይዙ አደርጋለሁ። አጋሬን ምቾት መንሳት አልፈልግምና በድንገት እንዲመጡ አልፈቅድም። መጀመሪያ እንደወጣሁ አካባቢ ቶሎ ቶሎ ሲመጡ ብዙም ቅር አልተሰኘሁም ነበር። ምክንያቱም እሷ የምትመጣበት ቀን ውስን ስለነበረ። ዝም ከአልኳቸው ግን ቶሎቶሎ መምጣትን ልማድ ያደርጉታል ብዬ ስላሰብኩ ከግዜ በኋላ ሰበብ መደርደር ጀመርኩ።
የለሁም፣ ክፍለ ሀገር ለስራ ሄጃለሁ፣ የመሳሰሉትን በማለት የመምጫ ጊዜያቸውን ቀነስኩት። ሲመጡም ሊጠረጥሩ የሚችሉበትን ነገር ሁሉ ቁምሳጥን ውስጥ ቆላልፌ ፊት ፊቱን ብቻ ነው የማሳያቸው።
ብቻ መኖር በጣም ደስ የሚል ነፃነት ነው ያለው። የራስ ስፍራ አለ፣ የፈለግኩትን መሆን እችላለሁ፣ በነፃነት ስልክ ማውራት እችላለሁ።
ራስን ለመሆን ነገሮችን የበለጠ ለመመልከት ነፃነት ይሰጣል ። ከዛ በተጨማሪ ውጪ ልጠራበት በማልችለው መንገድ አጋሬን ለመጥራት ነፃነቱ አለኝ። የእሷ ቤተሰብ ከኔ በተለየ ፈታ ያሉ ናቸው፤ እኔ ጋ ብትከርምም ምንም አይመስላቸውም ነበር። እኔንም ያቁኛል፤ የእኔም ቤተሰብ ያውቋታል። በየውኬንዱ አንድ ሳምንት እኔ፣ አንድ ሳምንት እሷ ጋር ነበር የምናሳልፈው። በአላት ሲመጡ እንሄዳለን። የእኔ ቤተሰብ ብዙ ጓደኞቼ ወንዶች ስለነበሩ እሷ የቅርብ ሴት ጓደኛዬ መሆኗን ስለተረዱ ደስ ይላቸዋል።
ቤተሰብ ጋ እያለን ገና የሆነ ጥያቄ የማያበዛ ልጅ አግኝተን ክፍል እንከራይ ነበር፤ ማደር ስለማልችል ቀን ገብተን ማታ እመለስ ነበር። ከሆነ ጊዜ በኋላ መጠራጠር ሲጀምሩ እንተውና overtime መስራት አለብኝ ብዬ እሁድ ስራ ማታ እመለስ ነበር። ከሆነ ጊዜ በኋላ መጠራጠር ሲጀምሩ እንተውና overtime መስራት አለብኝ ብዬ እሁድ ስራ ብዬ ወጥቼ ከሷጋ ተቀጣጥረን ፊልም እናይ ነበር።
ቤተሰቦቼ ቢያዉቁ አያቴም ብታውቅ እና ቢቀበሉኝ ደስ ይለኝ ነበር ግን አያቴም ቀጥታ እንደምትሞት እነሱም መቼም እንደማይቀበሉኝ አውቀዋለሁ። ስለዚህ ርቀቴን ጠብቄ የራሴን ህይወት እኖራለሁ።
ምንም ርቀቴን እየጠበኩ ቢሆንም በህይወቴ ውስጥ አሉ፤ ስፈልጋቸው መኖራቸውን ማወቁ ራሴ ሰላም አለው። ካወቁ ግን እንደማይኖሩ ስለማውቅ ቆርጠው እንደሚጥሉኝ ስለማውቅ ህመም ይፈጥራል።
በጣም በቅርብ አባቴ ልደቴን ሳከብር አታገቢም እንዴ ብሎ ጠየቀኝ፣ እስከዛ ድረስ በፍፁም ጠይቆኝ አያውቅም። ቆጣ ስል “ቀልዴን ነው” ብሎ ቢያልፈውም ለእህቴ ደውሎ ግን “ሴት ማግባትም ከፈለገች ለምን አታገባም?” ብሎ ጠይቋት እንደነበር ነገረችኝ። ያው እኔን ለማወጣጣት እንዲህ ቢሉም እውነታው ግን ሁሉንም ከኔ ሲያዉቁ ሙሉ ለሙሉ ከህይወቴ እንደሚወጡ ማወቄ ነው።
ስለዚህ የሚፈልጉትን ሆኜ ነው የማሳያቸው፤ ይህ ደግሞ ከልጅነቴ የተካንኩበት ነው። ሳገኛቸው አለባበሴን ሳይቀር ተጠንቅቄ ነው። ይህ የሚቀጥለው ግን አያቴ በህይወት እስካለች ድረስ ይመስለኛል ። ምክንያቱም ማስመሰሉ እኔንም ከአጋሬ ጋ ያለንንም ግንኙነት ይጎዳል።
እኔ ከድሮ ጀምሮ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባት የምፈልግ ሰው አይደለሁም። ከልጅነቴ ስለ relationship ጥሩ ነገር ሰምቼም አይቼም አላውቅም ነበር እና እንኳን ልገባበት ልፈልግ የማየው ትርምስ ራሱ ያስጠላኝ ነበር።
ከአጋሬ ጋር ፍቅር ውስጥ የገባሁ ሰሞን ከቤት ለመውጣት እንኳን ችግር ነበር፤ ሁለተኛዲግሪዬን የማታ መማር ስጀምር ነው የተወሰነ የመንቀሳቀስ እድል ያገኘሁት። እንደዛም ሆኖ የምወጣበትን ሰዓት ስለሚያዉቁ ቁጥጥሩ ኃይለኛ ነበር። እኔ ግን እሷን አግኝቼ ስመጣ የነበረው ስሜት ንትርኩን፣ጥቅጭቁን እና ውርጅብኙን ሁሉ ለመቋቋም አቅም ይሰጠኝ ነበር።
እኔ እና እሷ በባህሪ በጣም የተለያየን ሰዎች ነንግን አንድ ላይ ስንሆን የተሻለ ሰው ነው የምንሆነው። እኔ እድሜ ልኬን የዚህ አይነት ስሜት ይሰማኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ዛሬም ገና ስንጀምር የነበረው የፍቅር ስሜት ነው ያለኝ ለእሷ። እኔ ከስራ ወጥቼ ቤት የምትጠብቀኝ ቀን ከሆነ ደግሞ የሚሰማኝ ስሜት ልነግረው ከምችለው በላይ ነው። በጣም እናወራለን፤ እርስ በእርስ እንከባበራለን። የምንደባበቀው ምንም ነገር የለም። እንተማመናለን። በዋነኝነት የማያልቅ ራሱን የሚያድስ ፍቅር በመሀከላችን አለ። ሌላው የሚያስፈልገው የምትፈልገውን ነገር ማወቅ እናመረዳት ነው። ከእሷ ተለይቼ ሌላ ቦታ ብሄድ ከዚህ የተሻለ ነገር እንደማላገኝ አውቀዋለሁ።
ትዳር ለእኔ ፊርማ ወይም ወረቀት አይደለም። አይደለም አብሮ መኖሩ፣ መተሳሰቡ እና ህይወትን አብሮ መምራቱ ነው። በእሷ በኩል ያሉ ነገሮች ሲስተካከሉ አብረን እንደምንኖር አስባለሁ። የግድ መሆን ካለበትም የምንወጣበትን መንገድ ማግኘት እንደማይከብደን አምናለሁ።አንድን ሰው ስትወደው ነገሮች እንዲሰሩ የምታደርግበት መንገድ አታጣም። አብሮ ላለመሆን ምክንያት ለመደርደር ከታሰበ ሚሊየን ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ጎረቤት ያወራል ብንል እና አብረን ስንኖር አይተው እነዚህ ልጆች ቢሉ የእኔ ህይወት ላይ የሚጨምሩት ነገር የለም። ነገ የምንለያይ ነን አላውቃቸውም። እነሱም እኔም ዳግም ላንገናኝ ጉርብትና ሊቀር ይችላል። ለምንድነው ስለ እነሱ ሀሳብ የምጨነቀው? ቤተሰብም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። የተሳሳተ ነገር አላደረግንም ለምንድነው ስለ እነሱ ሀሳብ የምጨነቀው? ቤተሰብም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። የተሳሳተ ነገር አላደረግንም ምናልባት አውቀው ሌላ ነገር የሚሉ ከሆነም ያን ያህል የምረበሽበት ጊዜ ላይ አይደለሁም። የማስበው አንድ አለአያቴ እንጂ ስለሌሎቹ አይደለም። ምናልባት ብዙ ነገር ታጣለህ እኮ ግን የምወደው ሰውን ከማጣት አይበልጡም።
ስለምንፈልገዉ ነገር ማወቅ እና መረዳት አለብን ቀጣዩ ለዛ ስኬት መስራት ነው። ቀላል አይደለም ዋናው አስተዋይ መሆን ነው።
ብቻ ለእኔ በግሌ የኩዊር፣ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር የምለው አይደለም የሆነ ስያሜ ልሰጠው አልፈልግም። አንድ ሰው ሌላን ሰው ከወደደው ያ ቃላት ሊገልፁት የማይችሉት ስሜት ነው።
በእኛ ኮሚዩኒቲ ሲሆን በርግጥ ክብደቱ እና ትግሉ ከባድ ያደርገዋል። ከዛ በተጨማሪ አብዛኛው ሰው ከሀይማኖት ሁሉ ሊርቅ ይችላል። ይህ ውስጣችን የሚሰማን የስህተተኝነት ስሜት ይመስለኛል፤ ኃጢአት እያደረግን እንደሆነ የሚያደረግ አስተሳሰብ አለው፤ ግን ይህን ስሜት ማሸነፍ ከተቻለ ድንቅ ነው።
ሰው እያፈቀርክ እንጂ ያለኸው ኃጢአት እያደረግክ አይደለም። ለእኔ በህይወቴ የማልፀፀትበት ነገር ቢኖር እራሴን መቀበሌ ማህበረሰቡ ቤተሰብ ገፍቶኝ የማልፈልገው ህይወትውስጥ አለመግባቴ ነው። አሁን ላይ ደስተኛ ነኝ፤ መውጣትብችል እና ሰው ቢያውቅልኝ ደስ ይለኝ ነበር ግን እሱም ባይሆን በቤቴ ውስጥ ሆኜ ደስተኛ ከሆንኩ በቂ ነው።