እድገቴ ሞባይል፣ ኢንተርኔት የመሳሰሉት ብዙ ገነው የወጡበት ጊዜ አልነበረም። እንዳሁኑ አጥፏቸው ግደሏቸው የሚሉ መልዕክቶች የሚበዙበት ጊዜ አልነበረም። ትዝ ይለኛል ሰባተኛ ክፍል እያለሁ ነው ስልክ እየተለመደ የመጣው። የጥላቻ ንግግር ብዙ ሰምቼ አላውቅም ነበር። ባይሆን ሀይስኩል ሰገባ ጓደኞች እርስ በእርስ መላፋት ሲጀምሩ እንደ ቀልድ “ያ ነገር ነህ እንዴ?” መባባል’ን ሰማሁ። የከረረ ነገር ሆኖም ባይሆን ለቀልድ ብቻ እሱን እንደሰማው አስታውሳለሁ ከዛ የተለየ ነገር አልነበረም።
አንድ የማስታውሰው የሆነ የአዲስ አበባ ጉዶች የተሰኘ መፅሐፍ ነበረ፤ እዛ ላይ አንዳንድ ነገሮችን አንባቢያለሁ፤ ያም የሆነው ዜጋ ምን እንደሆነ ወይም ራሴን ራሱ ሳላውቅ ነበር። ከዛ በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ አንድ የኦርቶዶክስ ሰባኪ ስላወራቸው ዜጎች ይናገር ነበር እና የእሱን ወሬዎች ስምቻለሁ፤ በሰአቱ ነኝም ብዬ ስለማላውቅ ከራሴ ጋር ሳላገናኝ ነበር የምሰማው። መንፈስ ነው፣ ኢሉሚናቲ፣ 666 የሚባሉ ወሬዎችም በስፋት ይዛመቱ ነበር።
መቼም ከሃያ ምናምን አመት በፊት የነበረ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ እያስታወስኩ መናገር ቢከብደኝ ልጅነቴ ግን ዝም ያለ እና ቁጥብ ያለ እንደነበር አልዘነጋም። ከልጆች ጋር መጫወት ጭራሽ የማይሆንልኝ ነገር ነበር፣ እነሱ የሚጫወቱት ጫወታ አካላዊ የሆነ ወንዶች ልጆች የሚዝናኑበት ነገር ሁሉ ለእኔ ደስ አያሰኘኝም ነበር። ንፅህናዬን መጠበቅ እወድ ስለነበር ልብሶቼ ጭራሽ አይቆሽሽሹም ነበር። በብዛት ቤት ውስጥ ነው የማሳልፈው፣ በበለጠ ከሴቶች ጋር አግባቦት ነበረኝ። እውነት ለመናገር የልጅነት ትውስታ ብዬ የማስበው እንዲህ የሚባል የለኝም:: ጉርምስና ሲመጣ ወንዶችን በበለጠ የማየት ነገር ነበረኝ፤ እንዲሁ አድናቆት ነበር የሚመስለኝ። ልጅ ሆኜ ምንም ስለራሴ የተገነዘብኩት ነገር አልነበረም። አልፎ አልፎ የሚነሱብኝ ተባራሪ ጥያቄዎች ነበሩኝ፣ ግን ቆም ብዬ ለማሰብ ጊዜም አልሰጠኋቸውም ነበር። ወንድ ሳይ መደሰቴ እና አድናቆቴ ትንሽ ግራ ያጋባኝ ነበር።
እያለ እያለ ካምፓስ ገባሁ እና እንደ እኔ ስሜት የነበረው አንድ ሰው ተዋወቅኩ። የመጀመሪያዉን አመት ከእሱጋራ አብረን ሆንን። እሱ የካምፓስ ሰው አልነበረም ። በድፍረት ቀርቦ ያናገረኝና ስለ ፌስቡክም ያስረዳኝ ራሱ ነበር። መንገድ ላይ “ሀይ ቆንጆ ታምሪያለሽ ” ምናምን ብሎ በዚህ ሀገር ላይ በማይታመን ሁኔታ ነበር ያናገረኘ። አሁን ራሱ ሳስበው “የዛ አይነት ድፍረት አለ እንዴ?” ብዬ እደነቃለሁ።
ስለ ማህበራዊ ሚዲያ መኖር ሁሉንም ነገር ያስረዳኝም እሱ ነበር። ይህን ልጅ ሳስብ እድሜዬም ጨምሮ ስለነበር ለእሱ ያለኝ ስሜት ራሴን እንድጠይቅ አደረገኝ። ከእሱ ጋር ከተለያየን በኋላ ከማህበራዊ ሚዲያ ውጪ ሌላ ሰው ተዋወቅኩ ይህኛው ደግሞ ፌክ አካውንት እንድከፍት እና ዜጋ ምን እንደሆነ ያስረዳኝ ነው። ከዛ በፊት እኔን የሚመስሉ ሰዎች በውጪው አለም እንደሚኖሩ አውቅ ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ግን አላውቅም ነበር። እና ለረጅም ጊዜ “እኔ ብቻ ነኝ” የሚል አመለካከት ነበረኝ፤ እነዚህን ሰዎች ሳገኝ ምናልባት ብቻዬን አይደለሁም የሚለው አመለካካት ተፈጠረ ማለት ነው።
ነገር ግን ከመጀመሪያው ልጅ በኋላ ራስን የመጥላት ትግል ውስጥ ገብቼ ነበር፤ እንደሁላችንም የትኛውም ሀይማኖት አይፈቅድም በሚል ትግል እሰቃይ ነበር፣ ከማህበረሰቡም የሚሰማው ነገር ጥላቻ ነው እና ለምን እንደዚህ ሆንኩኝ በማለት ፈጣሪ እንዲለውጠኝ እመኝ ነበር። ስሜቴ ምን ማለት እንደሆነ አለመረዳት እና ፀፀት ነበረኝ።
ራሴን ወደ መቀበል የመጣሁበትን ሳስታውስ ከላይ የጠቀስኩት ፌስቡክ ያስከፈተኝ ሰው ሳገኝ እና የኮሚኒቲውን መኖር ስረዳ ብቻዬን እንዳልሆንኩ መገንዘብ ጀመርኩኝ፤ ይሄ ደግሞ የተወሰነ ሸክም አቀለልኝ።
የኮሚኒቲውን መኖር ስረዳ ብቻዬን እንዳልሆንኩ መገንዘብ ጀመርኩኝ፤ ይሄ ደግሞ የተወሰነ ሸክም አቀለልኝ። ከዛ በኋላ ነገሮችን ማጥናት እና ራስን የበለጠ በመረዳት የተሻለ አረዳድ ለራሴ ገነባሁኝ። ፌስቡክ ላይ 10 አመታት አስቆጥሬያለሁ፤ ሌላ ኩዊር ሰው ሳገኝ የነበረው ስሜት ብቻዬን እንዳልሆንኩ እና ስሜቴን የሚጋራ ሰው እንዳለ ነበር የተሰማኝ። አንድ ሁለት ሰዎችን በማውራት ጀመርኩ፤ ከጊዚያዊ ነገር የተለየ ነገር ባይሆንም ብቸኛ አለመሆኔ ብቻ በሰአቱ ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቶኛል፤ ራስን ወደ መቀበልም አድርሶኛል። የሚመስሉኝን ሰዎች እና ፍላጎቴን የሚጋሩ ሰዎችን ማግኘት ማውራት የምችልበትን መንገድ ፈጥሮልኛል። ጓደኞች መስርቼበታለሁ በበለጠ ደግሞ ስለ ኮሚዩኒቲው እንድረዳ አድርጎኛል። ለኮሚዩኒቲው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን እንዳገኝም የረዳኝ ማህበራዊ ሚዲያው።
ፌስቡክን ጥሩ ጏደኞች አግኝቼበታለሁ፣ የሚመስሉኝን ሰዎች አወራበታለሁ፣ አስተማሪ ፅሁፎችን አነብበታለሁ፣ ከሰዎች ጋር እግባባለሁ፣ ጓደኝነት እመሰርታለሁ፣ በነገሮች የሚግባቡ የሚመስሉኝን ሰዎች አገኝበታለሁ። ድሮ ድሮ የተለያዩ ነገሮች ሼር አደርግ ነበር። የተቆራረጡ የራሴን ፎቶዎች እና የሚሰሙኝን ነገሮች አጋራ ነበር። መረጃዎች ካሉኝም እንደዛው።
አሁን ብዙም አክቲቭ አይደለሁም። በውስጥ ከምግባባቸው ሰዎች ጋር ኢቨንት ሲኖር መረጃ ለመላላክ ከአልሆነ የለሁም። ያው እንደየቅርበታችን ይወሰናል። ከሁሉም ሰው ጋር መቅረብ ትቻለሁ። በማደርጋቸው ነገሮች ላይ እጅግ ጠንቃቃ ነኝ፤ ደህንነቴን ከምንም የማስቀድም ሰው ነኝ። ገና የጀመርኩ ጊዜ ብዙም እንደ አሁኑ የሚያሰጋ ነገር የለም ነበር። አሁን ግን ካለው ነባራዊ ነገሮች አንፃር በጣም እጠነቀቃለሁ! እንደድሮው የሚዘጋጁ ኢቨንትም አሁን ላይ የሉም። ስለዚህ ብዙም የምንለዋወጣቸው መረጃዎች የሉም። በተጨማሪም በተቻለኝ መጠን ራሴን በተለያዩ የጤና ነክ ነገሮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እጥራለሁ፤ ይሄ ዜጋነቴንም ከመረዳቴ በፊትም የማደርገው ነበር፣ ስለ ኤችአይቪ እና የተለያየ አባላዘር በሽታ እንዲሁም የአዕምሮ ጤንነቴን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ እሰጣለሁ። በዚህም ምክንያት ኦንላይን ላይ ከማገኘው ድራማ ራሴን ለማግለል እሞክራለሁ!
ከማህበራዊ ሚድያ እና ዴቲንግ አፕ ትውውቆች በኋላ ደግሞ ዴት ይኖራል።
ከምንም ነገር በላይ በመጠንቀቅ አምናለሁ የቱ ጋ እና መቼ ምን መሆን እንዳለብን መረዳት አለብን። ዴት እየወጣሁ እንኳን የጥንዶች ወንበር ላይ ቦታ ጠፍቶ አስተናጋጁ እንኳን ቢመራን በጭራሽ አልስማማም። ያለንበትን ሀገር መረዳት አለብን፣ ውጪ አይደለንም፤ የምንጠላበትና ለግድያ የምንፈለግበት ሀገር ላይ ነው ያለነው። በመደበቅ አምናለሁ፣ ከምንለብሰው ከምናደርገው፣ ከምንመርጠው ነገሮች ጀምሮ ራሳችንን ከአደጋ መጠበቅ መቻል አለብን። ካልተመሳሰልክ ተብሎ ይገደል የሚባልበት ሀገር ላይ ነን።
የመጀመሪያዬ ዴት የተለየ አይነት ነገር አልነበረም። ተገናኘን፣ ዋክ አደረግን፣ መያያዝም ሆነ እንደምትፈልገው መሆን አይቻልም። ውጪ መገናኘትን ከተቃራኒ ጾታ አፍቃሪያን የሚለየው ይህ ነው፣ የምትደብቀው ነገር ነው የሚበልጠው፤ ምንም ብትፈልግ ቤት ውስጥ እስካልገባህ አትችልም። ስትተቃቀፍ ትሳቀቃለህ፤ ሁሉም የሚያስተውልህ ይመስልሃል። ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪያን የሚደግፋቸው ሲስተም አለ። ቤተሰብ ወይ የሀይማኖት ተቋማት ማህበረሰቡ በሙሉ ይደግፋቸዋል። ስለዚህ ወንድ ወይም ሴት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሲሆኑ የሚሳቀቁበት ነገር የለም።
መጀመሪያ ያገኘሁት ሰው ጋ ምንም ለማድረግ እፈራ ነበር ከማውራት ውጪ፤ ቤቴ ስገባ ግን ምንም ማድረግ እችላለሁ፣ አሁን እያደረኩትም ነው። ክለብ ገብተህ ራሱ ወይን ማዘዝ አትችልም ምክንያቱም ሊፈጠር የሚችለውን ነገር አታውቅም፤ ያስፈራል። እንደ ኩዊር ሰው ዴት ማድረግ አስቸጋሪ የሚሆነው ፍቅራችሁ ሙሉ ለሙሉ በመደበቁ ነው። ራስህን መሆን የምትችልበት ነገር የለም ስለዚህ የራስ ስፍራ ላይ እስክትገባ ድረስ ብዙ ተቆንጥጠህ እና ተሰብስበህ ነው። ፍቅር መልካም ነገር ነው በእኛም ኮሚኒቲ ቢሆን በብዙ ነገር ተቀይጦ ያለ ነገር ቢኖርም ፍቅር መልካም ነገር ነው። ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም ስለዚህ ህይወትን የሚጋራን ሰው ማግኘት እና መዋደድ መፋቀርን የሚቃወም ማንም የለም።
አዝናኝ የምለው ነገር አለ ብዬ አላስብም፤ የተደጋገመ ነገር ነው ያለው ከሴክስ የዘለለ ነገር ስላሌለ አብዛኛው ግንኙነቶች ተመሳሳይ ናቸው። ግን የማልረሳው አንዴ ተማሪ ሆኜ ከሆነ ልጅ ጋራ ተቀጣጠርን እኔ በጊዜው ምንም አፎርድ ማድረግ እንደማልችል ነግሬው ነበር። ገና ለገና ገንዘብ ፈልጌ የሄድኩ እንዳይመስለው ያለሁበትን ሁኔታ አስረዳለሁ። ያም ሰው ሰው ከተስማማ እና ለእኔም ለእሱም ጉዳት የማያመጣ ከሆነ እዝናናለሁ፤ ከከተማ ወጥቶ መዝናናት ምናምንም ሊሆን ይችላል፣ እና ምን ሆነ ከዚ ልጅ ጋ ተቀጣጥረን የያዝነው ክፍል ገባን። እኔ የማውቀው አስቀድሞ ከፍሎ እንደሚታደር ነው። ከዛ ልጁ ድንገት ተነሳና መጣሁ ብሎ ጠፋ። ባየው ባየው አይመጣም፤ ተነስቼ ልወጣ ስል ብር ክፈል አሉኝ፣ ኪሴ ምንም አልነበረም፣ ደነገጥኩ “ወንድሜ ነው ምን አጋጥሞት እንደሄደ አላወቅኩም” አልኳቸው። ትንሽ ቢያንገላተኡኝም እሱም እንደማይመጣ ሲገነዘቡ እንድሄድ ለቀቁኝ። የሚገርመው ከብዙ አመታት በኋላ ይህን ልጅ የሆነ ኢቨንት ላይ ተገናኝተን ይቅርታ ጠይቆኛል። ከዛ በኋላ ውስጣዊ ስሜቴ የሚለኝን አዳምጣለሁ የሆነ ነገር የምትረዳበት ነገር አለ (gut feeling )።
ብቻ መኖር ነፃነት አለው ነገር ግን ነፃነት አለኝ ተብሎ ደግሞ መረን መልቀቅ የለብንም ባይ ነኝ። ጓደኞች ስንጠራ ሆነ ራሳችንን ለመግለፅ የምንመርጥበት መንገድ ሳይቀር በጥንቃቄ የተሞላ ነው፤ ለምሳሌ ቤት የምንጋብዛቸውን ጎደኞች ለእኔም ደህንነት የሚጠነቀቁ ናቸው አይደሉም? የሚለውን ራሳችንን መጠየቅ፣ ጎረቤታችን ማነው? ሰፈራችን ውስጥ ማን አለ? የሚል ነገር ሁሌ ማሰብ አለብን። ደህንነት በባለቤቱ እጅ ነው ያለው። ስፍራ አገኘው ተብሎ እንደ ፈለጉ መሆን አይን ውስጥ መግባትን ያመጣል፤ በመጨረሻ አደጋ ላይ ይጥለናል። ሰው አስገብተህ እንደ ፈለግክ ስትጮህ፣ ማታ ረበሸኝ ብሎ የሚያደምጥ ይኖራል፤ ስለዚህ ማን እየሰማ ነው ማን እያየ ነው የሚለውን ሁሌ ጥበቃ ላይ መሆን አለብን። ምን ያህል privacy የሚጠብቅ ጓደኛ ነው ያለን? ከጎረቤቶቻችን ጋር ቀረቤታችን ምን ያህል የተወሰነ ነው? ዘው ብሎ ቤት የሚገባ ነው? ሳይደውል ሳያሳውቅ የሚመጣ ማነው? የሚሉትን ማሰብ ይፈልጋል ። ከተጠነቀቅን ለብቻ መኖር በጣም ደስ የሚል ነገር ነው። ራስህን ለመሆን አቅም ይሰጥሃል።
ከጓደኞችህ ጋር ለመገናኘት ስፍራ ይፈጥራል ከምትፈልገው ሰው ጋር የፈለግከውን መሆን ያስችልሃል፣ ነፃነት አለው! የፈለግኩትን ውጪ መልበስ የማልችለውን እየለበስኩ፣ ታኮየን እየተጨማሁ በቤቴ ጎርድድ ጎርደድ ማለት ትልቀ ነፃነት አለው! ኩዊር ጎደኞችን ሰብስቦ ምግብ ሰርቶ አብሮ መብላቱ መጫወቱ ውጪ የማይገኝ ደስታን ይሰጣል!
ከምዕራባውያን አለም አንፃር እኛጋ ያለውን ነገር ስታነፃፅር በጣም ነው የሚገርመው፣ አግብቶ መኖር ቤተሰብ መመስረት እንደሚቻል ያምናሉ፣ እኛ ሀገር እንደ እኔ ልምድ 90% የሚያህለው ዜጋ ራሱን የመቀበል ችግር ያለበት እና ስሜቱን ከማርገብ የዘለለ ወደፊት ያለውን አይቶ መፅናት አይችልም። እንደ ዜጋ እንደ ሀገር ብዙ የግንዛቤ ችግር ይታየኛል፤ ሰው ለመማር ጊዜ አይወስድም ያ ደግሞ ወደኛም ኮሚኒቲ የገባ ነገር በመሆኑ ስለ ሰዎች ማንነትን የሚረዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው። በቃ ከላይ ከላይ ነው ሁሉም ነገር፤ ራስን የመረዳት እና ሌሎችን የመረዳት ችግር በጣም አለ።
ክሮስ ድሬሰር ነኝ። Crossdresser መሆን ድሮ ድሮ የግል ኢቨንቶች ላይ … የምንፈልገውን ለብሰን እኔም ጓደኞቼም ዘና እንል ነበር፤ አሁን የዛ አይነት ኢቨንቶች የሉም ጊዜውም መልካም አይደለም፣ ስለዚህ መጠንቀቅን አስቀድማለሁ። አዎ ምናልባት የምለብሳቸው ነገሮች በትክክል ልለብሳቸው የምፈልጋቸው ላይሆኑ ይችላሉ ግን ራሴን አደጋ ውስጥ መክተት አልፈልግም። ቤት ውስጥ እንደፈለግኩ መሆን እችላለሁ ።
ዴት ስታደርግ እንኳን እራስህን መግለፅ የምትፈልግበት መንገድ ሌሎች ላይረዱት ይችላሉ ሁሉም ተመሳሳይ የመረዳት አቅም እና በቂ መረጃ የለውም። እንደእኔ ብቻ ሳይሆን አብረውኝ እንዳሉት ሰዎችም ራሴን
የመረዳት አቅም እና በቂ መረጃ የለውም። እንደእኔ ብቻ ሳይሆን አብረውኝ እንዳሉት ሰዎችም ራሴን የምገልፅበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዴ ማስረዳት በራሱ ነገሮችን ያወሳስባል። ያ ሰው ፍቃደኛ ከሆነ በትንሽ ትንሽ ነገሮች ራሴን መግለፅ እመርጣለሁ። ማንነትን ቶሎ ከአለመግፅ አንፃር ተቃራኒ ጾታ አፍቃሪው ማህበረሰብ ይቅርና በእኛ ኮሚዩኒቲ መካከል ያለው ጭፍንተኝነት ቀላል አይደለም። አዎ አሁኑ አሁን ለውጥ እየታየ ነው ኩዊር ኮሚዩኒቲ pronouns ከመጠቀም አንፃር እንኳን ደካማ ነው። ወንድ ሆነህ የምን አንቺ መባል ነው ይሉሃል፣ እኔ ከተውላጠ ስሞች ጋር ብዙ ችግር የለብኝም ግን እንደምርጫ ከቀረበልኝ አንቺታውን እመርጣለሁ። ይህም ተቀባይነቱ በጣም የወረደ ነው። እንደ cross dresser ራስን መግለፅ አለመቻል ከባድ ነው በተለይ አካላዊ ወንድ ናቸው የሚባሉት ሰዎች በሚለብሱት ልብስ ከመሆን ይልቅ የሴቶችን መልበስ አለመቻል መደበቅ አለው። ግን እውነት ለመናገር አላፍርበትም በመደበቄ የሆነ ብስለት ላይ ስትደርስ እንዲያስጨንቁህ የምትፈቅዳላቸውን ነገሮች መምረጥህ አይቀርም።
እንደ ኩዊር እንደምንፈልገው ባለመሆናችን ወይም ኮሚዩኒቲው ላይ ያለው የማንወደው ባህል እንዲጎዳን መፍቀድ እና አለመፍቀድ የምንችለው እኛ ነን። አዎ ይከብዳል ግን ዛሬ ራሳችንን ማኖር አለብን። ምናልባት እኮ የዛሬ 200 አመታት ሌላ ኩዊር ትውልድ በነፃነት ይኖራል ደግሞ መሆኑ አይቀርም። ድሮ ሴታሴት ለሚባሉ ወንዶች ያለው አመለካከት በጣም ይደብር ነበር። በእኛ ኮሚዩኒቲ እኔ ለሆንኩት ሮል ራሱ ደስ የማይሉ አመለካከቾች ነበሩ። ስለትራንስ ሰዎች ስለነን ባይነሪ የነበረው ግንዛቤ አሉታዊ ነው። አሁን አሁን ትንሽ ለውጥ አለ ብዬ አስባለው። ከእጠላቸዋለሁ ይልቅ ምርጫዬ አይደሉም የሚሉ አስተያየቶች መጥተው እየተቀየሩ ነው። ይህ ደግሞ በየጊዜው የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ስለሆነ ነው። ብዙ ይቀረናል ግን ደግሞ የተወሰነ ለውጥ አለ።
ለውጥ ዱብ ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ በቀስታ ጠብ ጠብ እያለ የሚመጣ ነው ስቃይ ህመም ይኖረዋል ግን ያለ ነው።
ነን ባይነሪ ሰዎችን የመረዳት ክፍተት አለ በዜጋው ኮሚዩኒቲ ሳይቀር ያለማታየት ነገር አለ። እነዚህ ችግሮች የፈለገ ያህል ቢኖሩ ነገሮችን መቀበል ሰላም ይሰጣል፤ ለችግሮች መገዛት ማለቴ አይደለም ይልቅ ችግሮችን እንዴት አቅጣጫ ማስቀየር እንዳለብን መረዳት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። ራስህን የምትሆንበት ቦታ የለም፤ ማንነትህን ተናግረህም የሚቀበልህ ወይ የሚረዳህ ሰው ቁጥርም አናሳ ሊሆን ይችላል። በገዛ ኮሚዩኒቲያችን እነዚህ ነገሮች የአዕምሮ ጤናችንን እንዲያውኩ መፍቀድ የለብንም። ሰዎች ሁሉ ካልተቀበሉኝ ተብሎ መጨነቅም የለብንም እንኳን ሰዎች እኔም ራሴን ለመቀበል ጊዜ ወስዶብኛል። ስለዚህ መታገል ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ነገሮችን ተቀብሎ ራስን ማኖርን መማር አለብን።
ኩዊርነትን ከተቀበልኩ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነበር እንደ ነን ባይነሪ ራሴን መረዳት የጀመርኩት። ማንነትን ማወቅ ደስ የሚል ስሜት ይሰጣል፣ ከምን አይነት ሰዎች ጋር ዴት ብናደርግ ነው በተሻለ መልኩ የአዕምሮ ጤንነታችንን መጠበቅ የምንችለው የሚለውን ነገር ጭምር እንድረዳ አድርጎኛል።
ምክንያቱም ሁሉም ሰው ደጋፊ አይደለም ሁሉም ሰው ያለው መረዳት እኩል አይደለም ስለዚህ ለአዲስ ነገሮች ክፍት ቦታ ያላቸውን ሰዎች መርጠን ጊዜ ማሳለፍ አለብን። የአእምሮ ጤናችን ላይ ችግር እንዳይፈጥር ተቀባይነት የማጣት ወይም መኖራችን አለመታወቁ ተደብቀን እንድንቀር የሚያደርገን አካባቢ ላይ አለመገኘትን እንድችል አድርጎኛል።
ባጠቃላይ ማንነታችንን በሙላት መረዳትን እና በተሻለ መንገድ ህይወትን የመምራትን አቅምን ይሰጣል።