ፍቅራችን ነጻነት ቢጨመርበት ምን ያህል እንደሚጓዝ 

ውልደቴም እድገቴም አዲስ አበባ ውስጥ ነው። በቤተክርስትያን ውስጥ ያደግኩ በመሆኔ በእምነቱ በጣም ጠንካራ የሚባል ልጅ ነበርኩ። የልጅነት ህይወቴ በዓለማዊው እና በመንፈሳዊ ትምህርት የተቃኘ ነበር። ከጠዋት 3-9 በት/ቤት ከ11-1 ሰዓት ደግሞ በቤተክርስትያን አሳልፍ ነበር።

 

የልጅነት ትውስታ እምብዛም ባይኖረኝም በሆነ ወቅት 5ኛክፍል ላይ ከአንድ ወንድ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ጋር ልዩ ቅርርብ ነበረን። ይሄ ቅርርባችን ለሱ የተለመደ የጓደኝነት ሲሆን እኔጋ ግን የነበረው ስሜት የፍቅር ነበር። ምናልባት ፍቅርንም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነቴንም ያወቅኩት ያኔ ነው። ከሰኞ እስከ አርብ ብቻ የመገናኘት እድል ስለነበረን፤ የእሱ ሰፈር ከእኛ የሁለት ታክሲ ርቀትም ስለነበረው ለመገናኘት እድሉ ጠባብ ነበር። አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት ከእናቴ አስር ብር ወስጄ ኳስ የሚጫወትበት የሰፈራቸው ሜዳ ሄጄ ተደብቄ ሲጫወት አይቼው ነበር። የአጋጣሚ አቃጣሪ ግን አክስቴ እሱን ተደብቄ የማይበት ቦታ ላይ ይዛኝ እንዴት እንደመጣሁ አፋጥጣ ጠየቀችኝ። በሰአቱ ደንግጬም ቢሆን እግዜር ረድቶኝ “በሰንበት ትምህርት ቤት ኳስ ልንጋጠም መጥተን ነው” በማለቴ ተረፍኩ።

 

በተለያየ ጊዜ የኔ አይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች ወንዶችን የሚደፍሩ እንደሆኑ ፥ በዚህ ችግር ምክንያት ብዙ ወንዶች ሰገራቸውን በአግባቡ ማስወገድ እንደሚከብዳቸውና ከሰውነታቸው ትል መሰል ነገሮች እንደሚወጡ፣ ከጤና ባሻገር ደግሞ በሃይማኖት ፍጹም ውጉዝ መሆኑንና አስቀድሞ ፈጣሪ እኒህን ሰዎች በእሳት ዝናብ እንደቀጣቸው የሰይጣን፣ በተለምዶ የ666 ተላላኪዎች፣ የአውሮፓውያንን አላማ ለማሳካት የተመረጡ መጥፎ ማህበረሰብ ተደርገው እንደሚወሰዱ ስሰማ ነበር ያደግኩት። ስለዚህ ሌሎችም ጋር ይኖራል ብዬ እንደማስበው እኔም ጋር ይህ ፈተና ቀላል አልነበረም። ነገሩን እንደሃጥያት ከማሰብ የተነሳ ከዚህ ሃጥያት ያነጹኛል ብዬ የማስባቸውን ንስሃ፣ ጠበል መጠመቅ፣ ሱባኤ መያዝ፣ ቅዱስ ቁርባንን መሳተፍ፣ የመሳሰሉትን ሁሉ በመሞከር ከዚህ ህይወት ራሴን ለመለየት ሞክሬያለሁ። በአንዱም ግን ከዚህ ህይወት ሳልወጣ ቆይቻለሁ። ትግሉም በቀላሉ የሚነገርና የሚታለፍ አልነበረም ።

 

ለወንድ ልጅ የሚሰማኝ ስሜት ከተማርኩትና ከኖርኩት፣ ከሃይማኖትና ባህል ጋ ሲጋጭ በነበረኝ ከራስ ጋር የተፈጠረ ጸብ ምክንያት ለመውጣትና ለመተው በማደርገው ጥረት ውስጥ በነበረው መለወጥ ያለመቻል ጉዳይ በቃ እኔ እንዲህ ነኝ ወደሚል ድምዳሜ እንድደርስ ረድቶኛል።

 

አሁን ላይ ራስን የመቀበል ችግር ባይኖርብኝም አንዳንዴ በህይወቱ ውስጥ በሚስተዋለው ከባድ ጫና ምክንያት ያለሁበት ህይወት ከመሰረቱ ስህተት ይሆን እንዴ ብዬ እንዳስብ የምገደድበት ሁኔታዎች አይጠፉም።

 

ማህበራዊ ሚድያ ከልጅነቴም ጀምሮ እጠቀም ነበር። ማንነቴ ሳይታወቅ ገለል ብዬ ከመጠቀም ውጭ የተለየ የማደርገው ነገር አልነበረም። የኩዊር አባላትን ሳገኝ እጅግ ደንቆኝ፣ ገርሞኝም ነበር። ከምንም ነገር በላይ ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንዳስብ ረድቶኛል። በእውነቱ ማህበራዊ ሚድያን ባልጠቀም ብዙ ነገሮችን የማወቅ እድሉ አይኖረኝም ነበር። በማህበረሰባችን queer እና Lgbtq የሚባሉ ስያሜዎችን እንኳን እንዳውቅ የረዳኝ እና በአጠቃላይ ከስሜቴ ውጪ የኩዊር ነክ እውቀቶቼ ሁሉ መነሻቸው ከዚሁ ማህበራዊ ሚድያ ነው።

 

ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅኩትን ሰው በአካል ለማግኘት ቀጥሬም አውቃለሁ። ያንን ሰው ለማግኘትም በቦታው ቀድሞ ደርሶ ነበርና ከርቀት ሳየው በእድሜ ከእኔ ሰፊ ልዩነት ስለነበረው መሄዴን ሳልነግረው በድንጋጤ ተመለስኩ። ምክንያቱም ትልቅ ሰው በዚህ ህይወት ውስጥ ያለ ስለማይመስለኝ ነበር።

 

ስኬታማ የዴቲንግ ገጠመኝ ያለኝ ግን በአካል ከተዋወቅኩት ሰው ጋር ነው።

 

ስኬታማ የዴቲንግ ገጠመኝ ያለኝ ግን በአካል ከተዋወቅኩት ሰው ጋር ነው።
5ኪሎ የምከታተለው ትምህርት ነበረኝና ረፍዶብኝ ተጣድፌ አንዱ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ተቀመጥኩ፣ ታክሲው ቢሞላም ረዳቱ መጥራቱን ቀጥሏል፣ ሦስት ሦስት አድርጎ ሊያስቀምጠን ስለመሠለኝ፤ ተጠጋ ሳልባል ቀድሜ ጠጋ ብዬ ስቀመጥ አጠገቤ የተቀመጠውን ሰው ለመጀመሪያ ግዜ አስተዋልኩ።
እሱ ፊቱን ወደ መስኮቱ አዙሯል አያየኝም…”ተጠጋ” እንደማለት በዳሌዬ ገፋ ባደርገውም፤ ምንም ትኩረት አልሰጠኝም። በሰውነቱ የተነሰነሰው ሽቶ የሚማርክ ነበር፤ ስልኬን አውጥቼ አንድ ረጅም ጽሁፍ ላይ ብተከልም ልረጋ ግን አልቻልኹም ነበር። ሐሳቤን ሰረቀው፣ ላየው ፈለግኹ፣ ሙሉ መልኩን ማየት እና ምን አይነት ልጅ እንደሆነ ማወቅ ፈለግኩ፣ ድምጹስ ያምር ይሆን? እያነበብኹ አስመስዬ ቀና ሳልል አይኔ እስከደረሰበት የፊቱ ገፅታ ልቃርም ሞከርኩ፤ ነጭ ነጠብጣብ የታተመበት ሰማያዊ ሸሚዙ የቆዳውን መለስተኛ ጥቁረት አጉልቶታል። ከአየሩ ኹኔታ ጋር የሚሄድ ጥቁር ቡትስ ቆዳ ተጫምቷል። ማንበቤን ትቼ የእሱን ሁኔታ ማንበብ ተያያዝኩ፣ ድንገት ተንቀሳቅሶ አንድ እግሩን ሌላኛው ላይ አነባብሮ ተመቻችቶ ተቀመጠ።

 

እያየሁት ስለነበር እቃ የሠረቅኹ ያህል ተደናግጬ ወደ ንባቤ ለማተኮር ሞከርኹ፤ ያቆምኩበትን ስፈልግ ረዳቱ እጁን ዘርግቶ “ጥግ ላይ ሂሳብ ?” አለ። ድምጹን ልሰማው በመኾኑ ደስ ብሎኝ ጆሮዬን አቁሜ ጠበቅኩ። “ስንት ነው” ብሎ ጠይቆ ዝርዝር ብር ከፈለ። ፈገግ ያለ ይመስለኛል፤ ድምጹ ለዛ ያለውና ማራኪ ነው። ድጋሚ ብሌኔን ወደ ግራ አጣምሜ ሰርቄ አይኔ እስከደረሰልኝ አየሁት…መፅሐፍ በእጁ ይዟል ግን አልገለጠውም ። ፀባዬ ለእኔም ያስገርመኛል፤ ልክ የሚፈልገውን ሲያደርግ እንዳደገ ልጅ፤ የኾነ ነገር ማድረግ ከፈለግኹ ፈለግኹ ነው ያንን ካላደረግኹ ረፍት የለኝም፤ መልኩን ላየው ፈልጌያለኹ ግን እንዴት? የለበሰው አለባበስ፣ የተቀባው ሽቶ፣ ከአመታት በፊት የተጣላሁትን የቀድሞ ፍቅረኛዬን ቁጭ ነበር ።

 

ወደነበረበት አቀማመጥ ተመልሶ ጀርባውን ከወንበሩ አስደግፎ ቀጥ ብሎ ሲቀመጥ አይን ለአይን ተፋጠን ቀረን። ፀጉሩ ፍሪዝ ተደርጎ በቅባት ሞቅ ብሏል። በእውነት የድሮ ፍቅረኛዬም የተለያየን ቀን እንዲህ ተመሳሳይ ነገር ነበረው፤ ያ ምስሉ ለረዥም ጊዜያት በሕሊናዬ ጓዳ እያጮለቀ የኖረ ነበር። ዛሬደግሞ የቀን ቅዠት ያህል በአካል ያየሁት ስለመሰለኝ ነበር እዚህ ልጅ ላይ ማፍጠጤ . . . እሱስ ግን ለምን ይሆን ያፈጠጠብኝ?

 

ረዳቱ እንደገመትኩት ለሦስት አስቀምጦን ጉዞ ጀመርን…በየመሐሉ ሰረቅ አድርጌ አየዋለሁ . . . ሐሳቡን መሰብሰብ ያቃተው ይመስል ስልኩን ያበራዋል ያጠፋዋል ፣ በመስኮት አሻግሮ ይመለከታል . . . ከመገናኛ፣ በሾላ፣ ኢንግሊዝ ኤንባሲ፣ ቀበና አድርገን አራት ኪሎ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ጋር ስንደርስ እሱ ቀደም ብሎ “ወራጅ” አለ፡፡ እኔም ወረድኩና እሱ እስኪወርድ ሰዓቴን አየሁ 45 ደቂቃ ያህል ትርፍ ደቂቃ ነበረኝ፣ መንገድ የጠፋበት ሰው ይመስል ዙሪያ ገባውን እየቃኘው ጠበቅኩት። እሱ ሌላ አንድ ወራጅ ከወረደ በኋላ ተከትሎ
ወረደ . . .ሲያየኝ እንደመደንገጥ ብሎ ወደ ድል ሐውልቱ አቅጣጫ መራመድ ጀመረ። ዛሬ ሳላወራው አልሄድም ብዬ ለራሴ ፣ ተከተልኩት. . . ስሙን አላውቀውም ማን ብዬ ልጥራው? “አባት አባት” ሰምቶኝ
ዞረ፤ የማላውቀውን ሰው አናግሬ አላውቅም። ምን ብዬ ላውራው ? ” እዚህ አካባቢ ሽሮቤት
ታውቃለህ? ( ለማውራት ብዬ እንጂ ሽሮ እንኳን ከፍዬ ቤት ውስጥ እንኳን ለመብላት የሚደብረኝ ሰው ነኝ ) “እ እኔንጃ ብዙም አላውቀውም”
“አሃ እዚህ አካባቢ መስለኸኝኮ”
“አይ ለጉዳይ መጥቼ ነው።
ሌላ ምግብ ከፈለግክ ግን ወደዛ ጋር አለልህ” ብሎ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር አቅጣጫ ጠቆመኝ . . . “ለመብላት እዛ ድረስ አይከብድም?”
” እኔ ለመብላት አይደል ከቃሊቲ እዚህ ድረስ የመጣሁት” አለኝ (ከትንሽ ፈገግታ ጋር)
ይሄን ጊዜ ጥርሴ እንደአይን ሊፈጥ ፈለገ ልቤ ን እንደመኮርኮር ተሰማኝ
“ለመብላት ከቃሊቲ?” ብዬ ሳቅኩ

“ለመብላት ከቃሊቲ?” ብዬ ሳቅኩ
“የምሰራው ያው ለራሴ ለሆዴ ነው ማለቴ ነው” አለ ፈገግ እንዳለ
“በነገርህ ላይ እኔም ቃሊቲ ነኝ” አልኩት
“እኔኮ ታክሲ ውስጥ ስታየኝ ጠርጥሬያለው” አለኝ ቀበል አድርጎ
“መተዋወቅ እንችላለን?” አልኩት እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ፤ እሱም አላሳፈረኝም።
“ይቻላል።” አለና እጁን ዘረጋልኝ ።ከደስታ ብዛት ፈገግ ብዬ”ናዝ ናዝራዊ እባላለሁ ” አልኩት ። “እሺ ባሂር እባላለሁ።” አለ እጄን ሳይለቅ።
“ቅድም አፈጠጥኩብህ አይደል ?
“አልሸመደድከኝም ግን”
“ፈተና የሌለው ነገር መሸምደድ አይሆንልኝም” አልኩ እየሳቅኩ።
“የሰው ፈተና አይበልጥም ብለህ ነው?”
እየተቀባበልን ስንኮማመክ “ተመቸሁት መሰለኝ” አልኩኝ በሆዴ።
“ካልሆነ ወይ ፎቶ ላንሳህና በደንብ ላጥናሃ” ብዬ ቢፈቅድልኝ እምቢ የማልለውን ነገር ጠየቅኩት
“tatoo አይሻልህም?” ብሎ ትንሽ ሳቀና “ግን ምን አስበህ ነው እንደዛ ያየኸኝ?” ብሎ ጠየቀኝ
“ምን ባክህ ከድሮ ፍቅረኛዬ፣ ማነው ከፍቅረኛዬ ወንድም ጋር ተመሳስለህብኝ እኮ…” አልኩት እዚህጋ ይሆነ ነጥብ እንደያዘብኝ ሳልረዳ አላለፍኩም። ( አሁን እንዲህ ይባላል?)
ልጁ የድሮ ፍቅረኛዬን ቢመስልም ግን ነገረኛ ቢጤ ነበርና አፉን ንሾል አድርጎ
” ታድያ ወንድሟን እየተከታተል ግዜ ከምታጠፋ አንደኛህን ራሷን ይቅርታ ብትጠይቅ አይሻልም?”
አለኝ። ይሄ ሁሉ ስላወራኝ ብቻ በጣም ነበር ደስ ያለኝ ወሬውእንዲቆም በፍፁም አልፈለግኩም ነበር።
“እኔ መች አጠፋሁ አልኩህ?” አልኩት አይኖቹን ለማየት እየጣርኩ።
ሳቅ አለና ” ያጠፋ ብቻ አደለም ይቅርታ የሚጠይቀው፤ የምትወደውን ላለማጣት አንዳንዴ ይቅርታ ትጠይቃለህ ።”
የምለው ቢጠፋኝም ማውራት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ቀጠልኩ. . . .
“መች እወዳታለኹ አልኹህ?” አልኩት ግራ እየተጋባሁ።
“ባትወዳት ነው ሁሉም እሷን የሚያስታውስህ?”
የግቢ ቅያሱ ጋር ስንደርስ “እኔ እዚህ ጋር ነኝ” አልኩት ቅር እያለኝ።
“ምግብ ምናምን ስትል የነበረውስ?”
“ቅድም ሰዓት ነበረኝ እድሜ ላንተ ሰዓቴን ጨረስክብኝ” አልኩት ለቀልድ።
“አልቀረብህም ተማሪ ነህ?” ብሎ ጠየቀኝ።
“አዎ ነገረኛ ከመሆን አይሻልም?” አልኩት ጥያቄውን በጥያቄ እየመለስኹ።
“ወንድሜ ጤነኛ ነህ ግን?” አለኝ እንዴት ወንድ ሁኖ ከወንድ ጋር እንዲህ ይሟዘዛል የሚሉት የሃገሬ ያልበሰለ የጾታ ንግግር ውስጡ እንዳለ ለማስታወቅ።
ችግሩ እኔ ቀድሜ ሊሸሽገው የፈለገውን ዜጋነቱን አውቄበታለሁ።
“ማነው ነገረኛ አንተ!” አለኝ እጆቼን ያዝ መታ አድርጎ እየሳቀ።
ይዞ መጨበጡ ሳያንስ፣ ለሌላ ጊዜ ልንገናኝ ተነጋግረን ስልክ ተለዋወጥን።

 

አራት የቀን ህልሞች አልፈው በአምስተኛው ቀን ደወለ። የመጀመርያው ቀን የለሆሳስ ንግግር እያደገ ሄዶ ቀን በቀን መደዋወል፣ በአንድ ታክሲ የ3 ደቂቃ በምትሆን ርቀታችን እየተጠባበቁ በአካል ማሳለፍ ቀጠልን፤ የመጀመርያ ቀን ግንኙነታችም በጣም ለአጭር ሰዓት ነበር፤ እኔም እርሱም በዛ ሰሞን ለቅሶ ላይ ነበርን፤ ናፍቆት ሲብስ ግን ተገናኘን፤ ያን ያህል የሚካበድ እለት አልነበረም። የታመቀ ፍቅር እና ናፍቆት ሁለታችንንም አቀርዝዞን ነበር። በእግራችን እየተራመድን አንዳንድ ጉዳዮችን አወራንና ቶሎ ተለያየን። ከዛ በኋላ ግን ቀን በቀን መገናኘት እና walk ማድረግ፣ አንዳንድ የሚታዩ ነገሮች ሲኖሩ አብረን መሄድ እና መሰል ነገሮች በጊዜ ሂደት እያደጉ መጡ። ቤተክርስትያን ለመጀመርያ ጊዜ የሄድነው እነሱ ሰፈር የነበረ የዝማሬ ፕሮግራም ነበር። ጎን ለጎን ሁነን እየዘመርን አሳለፍን። እኔ ብቻ ሳልሆን እሱም በቤተክርስትያን ውስጥ የኖረ መሆኑ፣ ሽብሸባው እና የእያንዳንዱን መዝሙር ግጥምና ዜማ ማወቁ ደስ የሚል ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር።

 

አሁን ከብዙ የህይወት ጉዳዮች እሱን የመጀመርያ ጉዳዬ እንዳደርገው ነገሮች አስገድደውኛል። ከህይወት መውጣትና መውረድ፣ ከመብረድና ቅዝቃዜዉ ይልቅ፣ ልብ ጋር የሚደርስ የሱ ፍቅሩ ንዝረቴ ነዉ። እኔና እሱ ተፈጥሮ ብቻነን። ቀስ ያለ፣ የማይረብሽ፣ በሕይወት ዘመን አንዴ ብቻ የሚከሰት አይነት።

 

የእኔ ዓለሜ ነው ብል ማጋነን አይሆንም። በሰፈራችን አናት ላይ ያለው የተራራ ጫፍ ላይተቀምጠን የሚያወራኝ እንደህፃን ልጅ ስስት ያለበት አስተያየቱ ለዚህ እማኜ ነበር። ተያይዘን የሸኘናት ፀሐይ፣ ያለፈችን ጨረቃ፣ ለመውደዴ፣ ለፍቅራችን ብዙ ምስክሮቼ ናቸው። በማህበረሰብ ውስጥ፣ በድብቅ የምንኖር፣ እጅግ ልዩ፣ በፈተናዎች መካከል፣ እጅጉን ተዋደን የምንኖር ሰዎች መሆናችንን ሳስብ ይህ ፍቅራችን ነጻነት ቢጨመርበት ምን ያህል እንደሚጓዝ በማሰብ እጅግ እገረማለው።

 

አሁን ራሴን የlgbtq+ ቤተሰብ አባል አንዱ ነኝ ብዬ የማስብና ይሄ ሃጥያት አልያም የተለየ መጥፎ ነገር እንዳልሆነ የማውቅ ሰው ነኝ። አንዳንዴ ግን ምናልባት ስህተት እየሰራን ቢሆንስ የሚያስብሉኝ ጉዳዮች አይጠፉም። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቴ ያለንበት የኩዊር ቤተሰብ አባላት ላይ ከሌላው በተለየ ዝሙት እና አመንዝራነት በግድ ሊደረጉ የሚገቡ እስኪመስል ድረስ የእለት ተእለት ህይወት መሆኑን ሳይ ነው። መልካሞች ብዙ ቢኖሩም ተደብቀዋል፣ የሚሰማቸውም እምብዛም የለም። አንዳንዶች የኛው ቤተሰብ ቢሆኑም ራሳቸውን የተቀበሉ አይደሉም። ከፈጣሪ የተጣሉ እና ህይወታቸውን ማቅናት የማያስቡ ቁጥራቸው ቀላል አይደሉም። ተመሳሳይ ፆታ ማፍቀር ወንጀል በሆነበት ሃገር ውስጥ የኩዊር አባል የሆነ ግለሰብ አንድ ሰው አይደለም። አንዱ ብቻውን በጣም ብዙ ሰው ነው። ቤት፣ ሰፈር፣ ሚድያ ላይ የተቃራኒ ጾታ አፍቃሪ መምሰል በራሱ ብዙ ማንነት ይጠይቃል። የኛ ህይወት አንድ እየተደበቁ፤ አንድ እየተገለጡ የሚኖሩት በመሆኑ ሚስጥረኞችም ተአምረኞችም ነን። ራስን የመደበቅ ህይወታችን ደግሞ ለመተማመን እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል። እነኚህ ከባድ ጫናዎች፣ ጥያቄዬን ይጠመዝዙታል፤ ባላሰብኩት ያውሉኛል ያለሁበት ህይወት ከመሰረቱ ስህተት ይሆን እንዴ ብዬ እንዳስብ የምገደድበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ከዛ ውጪ ግን ራስን ለመቀበል የማደርገው የተለየ ትግል የለም።

 

በቤተ እምነት ያለው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ነው። የሚፈጥሩት ስሜትም አንድም የበደለኝነት፣ የብቸኝነት፣ የተሸናፊነት ስሜት፣ እጅግ ከባድና ራስን ወደመጉዳት የሚያሳድግ ነው። በአንድ ወቅትቤተ ክርስትያን ውስጥ አብሬው የምማር ልጅ ይህን ህይወት ፈጽሞ የሚጠላው እና በራሱም ሆነ ሌሎች እሱን በሚመስሉ ላይ የጥላቻ ንግግር ሁሌ የሚያደርግ ልጅ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ግን በማህበራዊ ሚድያ የኩዊር አባል መሆኑን ማረጋገጥ ችያለሁ።

 

በእሱና በዚህ መሰል ክስተቶች ኩዊር ማህበረሰቡን አጥብቀው የሚቃወሙ ሰዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት ራሳቸው የኩዊር አባላቶች እንደሆኑ ለማወቅ ችያለሁ።
ያለሁበት ህይወት ሃጥያት አይደለም ብሎ ማመን ቢኖርም አሁን ባለኝ መተማመን ልክ እርግጠኛ አልነበርኩም። በስብከቶች መሃል የሚሰነዘሩ ቃላትም ወደ ዳግም ተጠራጣሪነት ይመልሱኝ ስለነበር የዴቲንግ ህይወቴ በራሱ በሃጥያተኝነት የተሞላ ነበር፣ በርግጥ በጊዜው ዴቲንግ ላይ እምብዛም ነበርኩ።

 

ቤተእምነቶች ቢያውቁት የምለው እኛን ለማውገዝ ከመቸኮል ይልቅ ማንነታችንን ቢያውቁልን፣ እኛ ገፍተን ጸልየን ያመጣነው ሳይሆን፤ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌያችን መሆኑን ቢረዱልን፣ እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚወድ ቢያስተምሩ፣ ከምንም በላይ እኛን ለማጥፋት የሚታገሉትን፣ የሰውን ልጅ ለማጥፋት የሚደረግ እንቅስቃሴ በፈጣሪ ዘንድ ውጉዝ መሆኑን ቢያስተምሩ እና ሃሳባችንን ቢረዱን ምኞቴ መሆኑን ነው ።

 

ያለንበት ሃገር ከ98% በላይ አማኞች ያሉበት በመሆኑ እድገታችንም በዚሁ ስለሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ደግሞ በአንድነት የዚህ ህይወት ተቃዋሚ መሆናቸው የሚያመጣው የራስ ጥላቻ እና ሌላ ተያያዥ ችግሮች ብርቱና ከባድ ናቸው።

 

እግዚአብሔርን ከማወቅ ቃሉንም በደንብ የተማርኩ ስለሆንኩ ይመስለኛል በሚገፉኝ ሰዎች መሃልም ሁኜ በቤተ እምነት ውስጥ ያለምንም ፍራቻ እንቀሳቀሳለሁ። መገኘት መቻሌ የፈጣሪ ልዩ ጸጋው ወዳጅ መሆኑን እንድደነቅበት እና ከነልዩነቴ የሚወደኝ አባት እንዳለኝ ኣንዳስብ አድርጎኛል። አሁንላይ ከመላመዴ የተነሳ ይመስለኛል የጥላቻ ስብከት ቤተክርስትያን ውስጥ ብሰማም ምንም አይነት ነገር አእምሮዬ ላይ አይፈጥርብኝም።

 

ምናልባት አንድ ቀን በዛ ሜዳ ላይ ወጥቼ “ይህ ስህተት ነው” ብዬ የምናገርበት ጊዜ እንደሚመጣ አስባለሁ። ሰዎች ከክፋት ወጥተው፣ እውነተኛ የፍቅርን በረከት ለመቀበል የሚመኙበትን ስብዕና ይዘው፣ ተባብረንና ተደጋግፈን ይህን ክፉ ዘመን አልፈን፣ ለብዙዎች እውቀታችንን ህይወታችንን በመድረክ ያለፍርሃት የምንገልጽበት ህይወት ይፈጠር ዘንድ ምኞቴ ነው።

 

በኔና በባሂር ህይወት የድብቅ ማንነታችን ባለንበት ሃገር ወንጀል ሆነና ሰዎችን ጓደኞች የማድረግ ሃሳብ ሁለታችንም ጋር እምብዛም ተቀባይነት የለውም። አንዳንዴ የምፈራው በመሃላችን ልዩነት ቢፈጠርና ምናልባትም የግድ የሰዎች ሃሳብ የሚያስፈልግበት ችግር ቢፈጠር በሁለታችን መሃል ያለ ሰው አለመኖሩ ጠባችን እያሳሳቀ እንዳያጠፋን ነው።

 

ያም በጸሎት ወይንምራሳችንን ጥፋተኛ በማድረግ ካልሆነ የሚፈታ አይመስለኝም።

 

ደግነቱ የባሂር ጠባይ ለግጭት የሚዳርግ አይነት አይደለም፣ ዝምብሎ የሚታዘብ ሁለት ሶስት ቀን አይቶ የሚናገር አይነት እርግት ያለ ልጅ ነው። መደማመጥ እና የልብን ሳይሰስቱ መተንፈስም አለ።

 

መዝሙሮችን ማድመጥ ቢወድም ቤተክርስትያን ግን እንደኔ አያዘወትርም። አልፎ አልፎ አብረን እንሄዳለን። ነጠላ መልበስ ቢወድም ሲለብስ ሌላ ልዩ ፍጡር ነው የሚመስለው። ቤተክርስትያን ለመሄድ ከወጣን በኋላ መንገድ ላይ ስንገናኝ የመጀመርያ ስራዬ ነጠላው ላይ የተዛነፈች ነገር ካለ ማስተካከል ነው። ሲለብስ የሚያምርበት ነጠላ መሃል መዛነፍን መመልከት ያናድደኛል። “ቲ ህጻን በስርዓት አለብስም?” እያልኩ ሁሌ ሳልሰድበው አልቀርም። “ፈጣሪ ውስጤን እንጂ በነጠላ የሚቀጣኝ መሰለህ?” ይላል እሱ በቸልታ እንደተከናነበ። ቤተክርስትያን ደጅ ላይ በጸሎቴመሃል አለ፣ እሱጋ መኖሩን የማውቀው በጸሎት መሃል ቀና ብለን አይናችን ተፈላልጎ ስንተያይ ነው። ያን ሰዓት ሁለታችንም ስለፍቅራችን እየጸለይን ነው ማለት ነው። አምላክም ይሰማናል። ብዙ የሚለያዩን የሚመስሉ ክስተቶች ተፈጥረው በሚደንቅ ሁኔታ በዝምታ፣ ከዚያም በመነጋገር ፈትተናል። ይሄ ጌታ በህይወታችን ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንደሆነ እንዲሰማን አድርጓል። ረዥም አመታትን አብረን ዘልቀን ለኛም ለማህበረሰባችንም ምሳሌ እንደምንሆን ይሰማኛል፣ እመኛለሁም። አምላክ እንደ ምኞታችን ያኑረን።

Published
Categorized as Amharic

Leave a Reply

Discover more from Yezare Abebawoch

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading