እኔ ግብረ-ሰዶማዊ አይደለሁም፡፡

በመጀመሪያ ይሄንን መንገር እፈልጋለሁ ግብረ-ሰዶማዊ መሆን ምርጫ ነው፤ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነት ግን ተፈጥሮ ነው። ከነ’ጌ ማንነቴ እግዚአብሔር ግሩም እና ድንቅ አድርጎ ነው የፈጠረኝ። የወንጌል ትልቁ መልዕክት ፍቅር ነው። እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ እየሱስ አለምን እንደወደደ እንዲሁ ነው የወደደኝ። ክብር ለስሙ ይሁን።

 

ማናችንም ለመወደድ ያስገባነው ማመልከቻ ያቀረብነው መስፈርት የለም፤ ግን እግዚአብሔር እንዲሁ የወደደውን ማንነት እንዲሁ መውደድ ትክክለኛ ነገር ነው። ማንም ሰው ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሆነ የሚቆጥር ከሆነ፣ ራሱን የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ባልንጀራውን ያለምንም መስፈርት እንደራሱ መውደድ አለበት። በቃ መጽሐፉ የሚናገረው ይሄንን ነው።

 

የአንድ ሰው እድሜ ያህል በብዙ ከታገልኩ በኋላ ኩዊርነቴን ለመረዳት ስወስን፣ ማሰላሰል ጊዜ የወሰደብኝ 6 ወር አከባቢነው፡፡ ይሄን 6 ወር ልክ እንደ መተላለፊያ ወቅት ነው የምመለከተው፡፡ ወደ ብርሃን የመጣሁበት፣ የተገለጠልኝ ወቅት ብዬ ነው የምወስደው፤ ምክንያቱም ራሴን ከተቀበልኩ እና ካወቅኩኝ በኋላ እየኖርኩት ያለው ህይወት ከበፊቱ በብዙ ብርሀን የተሞላ እንደሆን ስለመሰከርኩ።

 

August 29 2021 አርባዎቹን ሳስቆጥር ከብዙ ዉጣ ዉረድ ቧሃላ ራሴን የተቀበልኩበት ቀን ነዉ። በዛ ዕለት ፍራሼ ላይ እንደተቀመጥኩ ከብዙ ሀሳብ በኋላ ወሰንኩ። “መታገል በቃኝ!!!” አልኩ። በልጁ በኢየሱስ በኩል ከራሱ ጋር ያስታረቀኝ ጌታ እንዲሁ ከራሴም ጋር አስታረቀኝ።

 

ተፈጥሮዬ ዉበት፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ እና ጥበብ እንጂ ሰዎች እንደሚሉት ከፈረንጅ የተኮረጀ ሀጢያት ወይም ክፉ መንፈስ አይደለም። ይሔ ከገባኝ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባሳለፍኳቸዉ አራት አመታት የገነባኋቸዉ ጓደኝነቶች ፣ የሰራኋቸዉ ስህቶችም ሆኑ ልክ የሆኑ ነገሮች ፣ ያገኘኋቸዉ ልምዶች ሁሉ በረከቶቼ መሆናቸው ገባኝ። በየቀኑ እያበሰሉኝ እያሳደጉኝ እየሔዱ እንደሆነ ይሰማኛል። ለዚህም መረዳት ያበቃኝ የመጀመሪያው ነገር ያሳለፍኩት የትግል መንገዴ ነው።

 

ትግሎቼ፣ መንገዶቼ፣ ያለማቋረጥ የጸለይኩባቸው፣ መፍትሄ ይሆናሉ ብዬ የሞከርኳቸው ሙከራዎች፣ አገሪቱ ውስጥም ከዛም ውጪ ያሉትን ይረዳሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ነገሮች ሁሉ ሞክሬ ስለነበረ በስተመጨረሻ እንዲህ ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ፤ “ምናልባት እግዚአብሔር ብዙ ጸሎቴን መልሷል፣ ብዙ መልካም ነገርም በህይወቴ አድርጓል እና ይሄ ነገር ልክ ይሆን? ተፈጥሮዬ ይሆን? እንዲህ እየለመንኩት ያለው ልመና ልክ ያልሆነ ተማፅኖ ይሆን? “ ብዬ ማሰብና ማሰላሰል ጀመርኩኝ፡፡

 

የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሆኜ ለመፈጠር ያዋጣሁት ነገር የለም። እና በተፈጥሮዬ ልክ አይደለህም እባላለሁ?

 

ሰዎች እንደሚሉት ብዙ በልጅነቴ መገፋት፣ ጌይ በመሆኔ የደረሰብኝ ተጽዕኖ ወይም የስነልቦና ቀውስ የለም፡፡ በጣም በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ እና በጥሩ የቤተክርስቲያን ማህበር ነው ያደግኩት። በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ በልጅነቴም የገፋኝ፣ ያገለለኝ የለም። ሁላችንም እየተጫወትን፣ እየተራገጥን፣ ማንም የማንም ጉዳይ ሳይሆን በደስታ ነው የኖርነው። ከዚህ ከዚህ በመነሳት ራሴን መጠየቅ ጀመርኩኝ።

 

ምናልባት ራሴን ስቀበል እግዚአብሔርን ብበድልስ? ሀዋሪያ ጳውሎስ አንድ ከፍል ላይ እንደዚህ ብሏል፤ “ ስጋ መብላት ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ እኔ ለዘላለም ስጋ አልብላ” ግን ስጋ መብላት ሀጥያት ሆኖ አይደለም፥

 

መብላት ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ እኔ ለዘላለም ስጋ አልብላ” ግን ስጋ መብላት ሀጥያት ሆኖ አይደለም፥ ሌላው መሰናክል እንዳይሆን ነው እና እኔም ራሴን መቀበሌ ለሌሎች ሰዎች መሰናክል እንዳይሆን ፈራሁ። ቢሆንም ደግሞ ሰዎችን እንዳላሰናክል ራሴን አይደለም አለመቀበል ያለብኝ፣ ራሴን መግለጽ ነው የሌለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ። ምክንያቱም ካለሁበት ሁኔታ ወይም ካለኝ ሃላፊነት አንጻር እወነት ለመናገር የማጣው ነገር እንደሚኖር አወቅኩ።

 

በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ሰላለሁበት ነገር ቢያውቁ የማጣው ነገር ብቻ ሳይሆን የሚያጡት ነገርም አለ። እና በሰዎች ዘንድ ያለኝን ክብር እና ጥሩ እምነት ማጣት ስላልፈለግኩ ራሴን ብቀበልም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነኝ ብዬ ለመውጣት ግን አማራጬ እንዳልሆነ አወቅኩ።

 

ተፈጥሮዬ የማላደርገው እንጂ የሚያሳፍረኝ ተፈጥሮ አይደለም፡፡ መጽሀፍ ቅዱስንም ሳነብ በተለይ በጣም በዙ ሰዎች የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ለመውገር የሚጠቀሙበት ቃል ሮሜ ምዕራፍ ከአንድ እስከ 28 ድረስ አለ። “ሴቶችም ወንዶችም ፤ ለባህሪያቸውን የማይገባውን አያድርጉ” የሚል ቃል አለ። እውነት ለመናገር ራሴን ለመቀበል በጣም ትልቅ ቁልፍ የሆነኝም ቃል ደግሞ ይሄው ነው። ይሄን ቃል ካነበብኩ በኋላ በይበልጥ ማሰላሰል ጀመርኩኝ።

 

የኔ ባህሪ ምንድን ነው? ለባህሪዬየማይገባ ነገር ነው እየፈለግኩ ያለሁት? ለባህሪዬየማይገባ ነው እየተመኝሁ ያለሁት? ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ። እውነት ለመናገር ለባህሪዬየማይገባውን አይደለም እያደረግኩ ያለሁት፣ ለባህሪዬ የሚገባውን እንጂ እየተመኘሁኝ ያለሁት። ለ’ኔ ለባህሪዬ የማይገባው ነገር ሴቶችን ለፍቅር መጋበዝ ነው፡፡ ገና ለገና ከሰዎች ተቀባይነት ለማግኘት ከሴት ጋር የማይዘልቅ ግንኙነት ጀምሬ የሴቷን ህይወት ማመሳቀል፣ ህይወቷን እና፣ ትዳሯን ከባድ ማድረግ ነው ትልቅ ሀፂያት።

 

በየትኛውም ሴት ህይወት ውስጥ ችግር መሆን የለብኝም። የኔ ባህሪ የሚገባው ነገር ልክ እንደኔ ተመሳሳይ የሆነ ወንድ መውደድ ነው፡፡ ከምወደው ወንድም ጋር ተፋቅሮ መኖር ነው፡፡ እናም ይህ ቃል በትክክል ሃሳቤን እንድገልጽ፣ እራሴን እንድረዳ እና እንድቀበል የረዳኝ የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው፡፡

 

አብዛኛው ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ላይ ነው የማሳልፈው፡፡ በአገልግሎቴ ደስተኛ ነኝ፣ ብዙዎች ይጠቀማሉ ይባረካሉም እኔም እንደዛው፡፡ እና ራሴን መቀበሌ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቴ ተፈጥሮዬ በመሆኑ ምክንያት እግዚአብሄር የሰጠኝ በረከት አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሰዎች እንደዚህ አይነት ስሜት ብቻ ስለተሰማቸው የሚደርስባቸው ዱላ በንግግር እና በቃላት ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ጭምር በመሆኑ መከራው ብዙ ነዉ፡፡

 

ምናልባት እግዚአብሄር ለእነኚህ ሰዎችስ ቢሆን እኔን እዛ ቦታ ያስቀመጠኝ ብዬ ብዙ ጊዜ አስባለሁ፡፡ ልክ ዮሴፍን በምክንያት ወደ ግብጽ እንደወሰደው እኔንም ለእነኚህ ሰዎች ረፍት እንድሆን አዘጋጅቶኝ ቢሆንስ እላለሁ። ሰዎች ከእግዚአብሔር ቤት ሲገፉ የሚቀበላቸው የውጪው ዓለም የከፋ ነው። ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ ትክክል ባልሆነ ጊዜ ምናልባት ሊቀበልን ይችላል ብለው የሚያስቡበት ማህበር ጋር ነው የሚሄዱት ያ ከቤተክርስቲያን ውጪ ያለው ማህበረሰብ ደግሞ የምናቀው ነው፣ አለማዊ እልል ያለ አለማዊ ነው። ብዙ ዋጋ ያስከፍላቸዋል በእግዚአብሔር ላይ ቁጣ እንዲያነሱ፣ በሰዎች ላይ ቁጡ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ጠብቀው ለመቆየት ሲሉ አስቀያሚ ልምድ ውስጥ ይገባሉ። ያ ደግሞ ለሂወታቸውም ሆነ ለጤናቸው ዋጋ ያስከፍላቸዋል።

 

ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድ በእነርሱ መንገድ ያለፈ፣ ሊረዳቸው የሚችል ሰው ቢኖር ግን ትግላቸው ይቀንሳል። ራሳቸውን ለመቀበልም እድሜያቸውን አይጨርሱም። የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆን ካገኙት ሰው ጋር መጋደም ፣ ሰካራም፣ ዓመፀኛ፣ ተሳዳቢ፣ ቀማኛ መሆን

 

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆን ካገኙት ሰው ጋር መጋደም ፣ ሰካራም፣ ዓመፀኛ፣ ተሳዳቢ፣ ቀማኛ መሆን አይደለም፡፡ ልክ እንደ አንድ ተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ ለተመሳሳይ ጾታ የፍቅር ስሜት ወይንም የወሲብ ስሜት አለን ማለት ብቻ ነው። ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለውም። ልክ አንድ ሽብሬን እንደሚያፈቅር ሺበሺ የሚባለው ሰውዬ፤ ግርማን የሚያፈቅር ግርማ ማለት ነው። የትጋ ነው ነውሩ?

 

ስለዚህ ይሄን ስሜቱን ይዞ ከእግዚአብሄር ጋር መቀጠል፣ መጸለይ፣ የእግዚአብሄርን ቃል ማንበብ፣ ማገልገል ይችላል ማለት ነው። ለዛ ሰው ምቹ አካባቢን መፍጠር ማለት ነው። በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ይህንን ማድረግ ከባድ ቢሆንም ባለሁበት ቦታ በኔ ተጽእኖ ክልል ስር ቢያንስ ለአንድ ሰው መድሀኒት መሆን እችላለሁ ብዬ ስለማምን በአገልግሎቴ እና በስፍራዬ ፀንቼ አለሁ።

 

ቅድም እንደገለጽኩት በቤተክርስቲያን ያለኝ ቦታ ለኔ እንደ ጥሪ ነው። ምክንያቴም እዛ አከባቢ ያሉ ሰዎች ገና አዲስ የሚመጡ፣ ትንንሽ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ያገቡ፣ ትልልቅ ሰዎች የመሳሰሉት ናቸው። የትውልድ ጅረቱ እስከ ቀጠለ ድረስ አጭር፣ ወፍራም፣ ረጅም ሰዎች መወለዳቸው እንደሚቀጥል ሁሉ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሰዎችም መወለዳቸውን ይቀጥላሉ።ማንም ሰው ወደ ወደእግዚአብሄር መንግስት እንደሚመጣ ሁሉ፤ እነኚህም ሰዎች ወደ ወደእሱ ሊመጡ ይችላሉ ሲመጡ ግን ምቹ ቦታ ያስፈልጋቸዋል። 

 

ያንን ማዘጋጀት ደግሞ የኔ ሃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ። ስለራሳቸው፣ ስለ ጾታዊ ዝንባሌያቸው ስለሴክሹዋሊቲያቸው በተወሰነ መልኩ እኔ ልነግራቸው ካልቻልኩ ሚዲያ ይነግራቸዋል። ሚዲያው ደግሞ በጣም በተሳሳተ እና በተንሻፈፈ መንገድ ነው እኛን የሚያየን። እና ነገ እነኚህ ልጆች ጠፍተው ከማዘን ከመጨነቅ አሁኑኑ ምቹ ቦታ መፍጠር አለብኝ ብዬ አምናለሁ። 

 

ጸልያለሁ፣የእግዚአብሔርንም ቃል አነባለሁ፣ መዝሙር እወዳለሁ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቼ እና እህቶቼጋ አብረን መፅሀፍ ቅዱስ እናጠናለን፣ ይህንኑ የምናደርግበት ግሩፖች አሉን፣ አብረን ምሽግ እንገባለን።

 

 

እንደኔ የሚያስብ ሰው እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ አግኝቶኝ ቢሆን በጣም ብዙ ነገር በተሻለ መንገድ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም አንደኛ ራስን ለማጥፋት የሞከርኳቸው ሙከራዎች፣ በህይወቴ ተስፋ የቆረጥኩባቸው ነገሮች፣ በእኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ደግሞ ስለእኛ ማንነት የሚሰብኩትን ፓስተራችን በጣም በተደጋጋሚ እየመጡ የሚሰብኩትን ነገር ስሰማ ይጨንቀኝ ነበር። 

 

ከሰባኪዎቹ አፍ የሚወጣው ሁሉ ይዘገንናል። እና እያንዳንዱ የሚናገሩት ነገር ልክ እኔ መንገድ ላይ ስራመድ ከሰማይ እሳት ዱብ ብሎ የሚያቃጥለኝ እና የሚፈጀኝ እየመሰለኝ እሳቀቅ ሁሉ ነበር። የሚዘገንን ዲስኩራቸዉን በመስማት ከመሳቀቃቸው የተነሳ ጭራሽ ወደ ቤተክርስቲያን ዞረው የማይተኙትን ቤት ይቁጠራቸው። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ “አለሁልህ” ብሎየሚነግረኝ ሰው ቢኖር ነገሮች በጣም የተሻለ ይሆኑ ነበር ብዬ አስባለሁ። 

 

በተቃራኒው እንደ አንድ አማኝ ደግሞ ምን አምናለሁ ምናልባት የእግዚአብሔር ፍቃድ በዚህ መንገድ እንዳልፍ ሊሆን ይችላል። በባህሪዬ በጣም ፈጣን ከመሆኔ የተነሳ እዛ እድሜ ላይ ልቅቅ ያልኩ ብሆን ኖሮ ምናልባት አላስፈላጊ ልምዶች ኖረውኝ ራሴን አሁንም ላላገኘው እችል ይሆን ነበር ብዬ። እነዛ ራሴ ላይ በር ቆልፌ ያለቀስኩባቸውን ቀናቶች፣ ለመሞት የፈለግኩባቸውን ጊዜያቶች እግዚአብሔር በመልካም እንደለወጠልኝ ነው የማስበው። 

 

ሁለት በምክንያት ነው የሆነው ብዬ የማስባቸው ነገሮች ውስጥ፤ አንደኛው ወደ ኋላ ተመለሼ እንዳላይ እና sexualityዬን በተመለከተ “ልክ አይደለህም”ለሚለኝ ሰው ለምናገረው መልስ ከመረጃ ተነስቼ ሳይሆን ህይወቴን sexualityዬን በተመለከተ “ልክ አይደለህም”ለሚለኝ ሰው ለምናገረው መልስ ከመረጃ ተነስቼ ሳይሆን ህይወቴን ጨምቄ በሰራሁት ኤክስፐርመንት ነው። የመጣሁበት መንገድ፣ ያለፍኩበት መንገድ ነው ህይወቴን የፈተንኩት መርዝ እንደሚገድል በአይጥ ተመራምሮ ሳይሆን እኔ በራሴ ቀምሼ ሞክሬው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች ሰዎችን ለማጽናናት፣ ለማገዝ ይረዳል እና በአንድ ወቅት በእናንተ ጫማ ላይ ቆሜ ነበር፤ በዚህ መንገድነው ያለፍኩት ብዬ እንዳግዝ ያደርገኛል። 

 

ሁልጊዜ የማምነው ነገር፤ ልክ ያልሆኑ ድካሞቻችንን እንኳን እግዚአብሔር ለመልካም እንደሚጠቀማቸው ነው። ያለፍናቸውን አድካሚ ወቅቶች አሁን ላይ በምክር ለማግዛቸው ልጆች ሲጠቅም፣ ሌሎችም ሰዎች ሲጽናኑበት እና ሲማሩበት ስላየሁኝ ደስተኛ ነኝ። የመጣሁት መንገድም ብዙዎችን ያግዛል ብዬ ስላመንኩ እንደ ኪሳራ አልቆጥረውም። አሁን ላይ በጣም ደስተኛ ነኝ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ነፃ ነኝ፣ ቀና ብዬ ነው የምሄደው። አንገቴን ቀና አድርጌ I’m proud, happy, smiley, joyful, born again, loved and a gay Christian. የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ጠል ማህበረሰብ ያልገባቸው ነገር እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ በኢየሱስ ካጸደቀን የሚኮንነን ማን ነው?

 

 

አስታውሳለሁ እድሜዬ ለጋብቻ በደረሰ ጊዜ፤ ነፍሴ ወንድ እያፈቀረች አፌ እና አዕምሮዬ ስለሆነች ቆንጆ ሴት ያወራና ያስብ ነበር። እግዚአብሔር ለእኔም ለእህቶቼም ስለራራ ነበር የመሰረትኳቸው የፍቅር ግንኙነቶች ያልተሳኩት። ያም የተወሰነ ፋታ እንዳገኝ አግዞኛል። ለምሳሌ “ከሷጋር ስለተለያየ ሌላ ሴት ማየት አይፈልግም ልቡ ተሰብሯል አይነት…” ከዚህ በተለየ አልፈዉ እንዳገባ የሚጠይቁኝን የቤተሰብ፣ የቤተክርስቲያን እና የሰራ ቦታ ጓደኞች ሁሉ ደግመዉ በዚህ ጉዳይ እንዳያወሩኝ እንደየ ሁኔታዉ አስረድቻቸዋለሁ። አንዳንዶቹን በትህትና፣ አንዳንዶቹን ድንበር እያለፉ መሆኑን በማስገንዘብ፣ አንዳንዶቹን በመቀለድ፣ ሌላዉን በመሸሽ። የቅርብ ለምላቸዉ ሰዎች ግን ሚስት ማግባት እንደማልፈልግ እና አሁን ባለሁበት ሁኔታ ደስተኛ እና አመስጋኝ መሆኔን በመንገር ነዉ። በተለይ ባለሁበት ነባራዊ ሁኔታ የቤተሰብ ሀላፊነት፣ በቅርብ በሚያዉቁኝ ሰዎች ዘንድ ታማኝ እንድሆን አድርጎኛል። ሌላዉ ባህሪዬ እንደ አብዛኛዉ ጌይ ተንከባካቢ ለስላሳ እና ሁኔታዎችን ተረጂ ነዉ። እያንዳንዷተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ ሴት አንድ የልብ ጓደኛዋ ጌይ ቢሆን የተሻለ ህይወት የምትኖር ይመስለኛል። አገራችን ላይ ይህን ማድረግ ብርቅ ሆኖ ባይታሰብም። ይሔም ለስላሳ ባህሪዬ ብዙ ሴቶች ከኔ ፍቅር እንዲይዛቸዉ፣ በቤተክርስቲያን የሚያዉቁኝ ሰዎች ላላገቡ የቅርብ ሰዎቻቸዉ የሚመኙኝ፣ አልፎም የሚጠይቁኝ ሰዉ አድርጎኛል። (ወንዶቹ ብቻ ምን ሲሆኑ እንዳላዩኝ እግዚአብሔር ይወቅ ።) የሚጠይቁኝንም ሆነ የሚያስጠይቁኝን ሁሉ በትህትና በአክብሮት የጋብቻ ሀሳብ እንደሌለኝ እነግራቸዋለሁ። ምርጫቸዉ ስላደረጉኝም አመሰግናቸዋለሁ፣ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ በዚህ ሁኔታ እመልሳቸዋለሁ። እኔ ባለሁበት አነስተኛ የሆነች ቤተክርስቲያን የማይታወቅ ሰዉ የለም። የጫማዬ ቁጥር፣ የምግብ ምርጫዬ፣ ጸጉሬን የት እንደምስተካከል ሁሉ በሚታወቅበት (ያለማጋነን ነዉ) ቦታ “ዜጋ” ሆኖ መኖር አስጨናቂ ነዉ። ከረዥም የብቻ ራስ መቀበል ትግል ጉዞ በኋላ ሌሎች የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን ለማግኘት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ መጣሁ። እዛ ላይ ከራሴ ጋር እየታገልኩ በነበረበት ወቅት ሌሎችንም የትግል አጋሮች አብረን “እንድንፈወስ” ብዬ የከፈትኩት ነበር። ናኦድን የተዋወቅኩት እዛ ነበር። ከናኦድ ጋ የተገናኘነዉ አንድ ሌላ የጋራ ጓደኛችን በጻፈዉ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ሰንሰጥ ነዉ። ከዛዉ ተነስተን ማዉራት ጀምረን ጓደኞች ሆንን። ሁለታችንም በአጥቢያ ቤተክርስቲያኖቻን መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሰጥ በመሆናችን ለመግባባት አልከበደንም። ከዚህ በመነሳት እንጸልያለን፣ እንበረታታለን፣ ሴቶችን date ስለማድረግ እና ስለሌሎች የህይወት ጉዳዮች እናወራ ነበር። በመሀል ግን ናኦድ ከኣንድ ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙት ጀመረና ተጠፋፋን። አሁን እግዚአብሔር የባረካቸዉ ጥንዶች ሆነዋል።በጊዜዉ ግን “ከትግላችን አፈገፈግህ” በሚል ስሜት እንዲለያዩ በጣም እፈልግ ነበር። አሁን ላይ ለራሴም ለሌሎችም የምመኘው ህይወት ነዉ ያላቸዉ። በተለይ ለኔ ማረፊያዎቼ፣ በነጻነት ራሴን የምንሆንበት ቦታዎቼ፣ እንባ እና ሳቄ በነጻነት የሚፈነዳበት መጠለያዎቼ ናቸዉ። ማረፊያዎቼ፣ በነጻነት ራሴን የምንሆንበት ቦታዎቼ፣ እንባ እና ሳቄ በነጻነት የሚፈነዳበት መጠለያዎቼ ናቸዉ። ጥልቅ የወንድማማች እና ቤተሰባዊ ፍቅር ገንብተናል። ይሔ ደግሞ የኣዕምሮዬን ሰላም ከመጠበቅ ያለፈ ማንነቴን በድብቅም ቢሆን በኩራት እንድኖረዉ አግዞኛል። እኔንም በነሱም ሆነ በሌሎች ሰዎች ህይወት ዉሰጥ ጠቃሚ ሚና እንዲኖረኝ አግዞኛል።

 

አሁን ላይ “ራሴን ከተቀበልኩ በኋላ ለማህበረሰቤ ምን መስጠት እችላለሁ?” ከሚል እሳቤ ጋር ጠቃሚ መስሎ የሚታየኝን የራሴንም ሆነ ከሌላ ቦታ ያገኘሁትን ሀሳብ በማጋራት አጫጭር ጽሁፎችን በመጻፍ የምችለዉን ለማድረግ እየሞከርኩ ነዉ። ራሳቸውን መቀበል ያቃታቸው፣ በብዙ እርግማን ራሳቸውን ስለወጉ ለእግዚአብሔር የወገኑ ለሚመስላቸው ወገኖቼን፤ እሱ የሚወደው ይሄንን አይደለም ራሳችሁን እንድትወዱ እንጂ የሚሉ ጽሁፎችን እያጋራሁ እገኛለሁ።

 

“ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ! አይደለ የሚለው ሌላውን የመውደድ መለኪያ ራስ ነው። ለራሴ ያለኝ ፍቅር ነው ሌላውን የምወድበት። ለራሳችሁ ትክክለኛ የሚገባችሁን ቦታ ስጡ፤ እግዚአብሔር ይወዳችኋል። እናንተም እራሳችሁን ውደዱ” እያልኩ እጽፋለሁ። ማህበራዊ ሚድያ ያስገኘልኝ ነገር ቢኖር መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲህ የማግዛቸው (mentor) የማደርጋቸዉ እንደ ኣባትና ልጅ የምንተያይ ወጣት ልጆችን ማገልገል የምችልበት እድል በመኖሩ ነዉ።

በፌስቡክ ገጼ ላይ የምጽፋቸዉ መንፈሳዊነት ያላቸዉ ዜጋ ተኮር ጽሁፎች ስበዋቸው አሁን መልካም ጓደኛዬ የሆኑ ብዙ አሉ። 

 

አሁን ላይ ራሴን የማየው በታዳጊዎች እና በወጣቶች ላይ እንዲሁም አንድ ለኣንድ በተወሰነ ጤናማ ዘላቂ የፍቅር ግንኙነት(ትዳር) ላይ የሚያተኩር እንዲሁም ለማህበረሰባችን ነጻነት የሚችለዉን ሁሉ እንደሚያደርግ አክትቪስት ነዉ። በአንድ ወቅት በብዙ የህይወት ጉዞ ውስጥ ካሉ የኩዊር ልጆች ጋር የመገናኘት እድሉን አገኘሁ። በጣም አለቀስኩ! አንዱ ደስታ ነዉ፤ ራስን በሌሎች ማግኘት። ሁለተኛዉ ምነዉ በእነሱ እድሜ እኔም እንዲህ ሰው ኖሮኝ ቢሆን እላይ ከአነሳሁት ስሜት ነው። ለተተኪው ትውልድ፣ ላገኘኋቸው ወጣቶች ሁሉ ደስ አለኝ።

 

 

በዚህ ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔርን የማመሰግነዉ ያን ያህል የሚጎዳ ነገር በማህበራዊ ሚድያው አልገጠመኝም። ያ ማለት ግን ሁሉ ሰላም ነው አይደለም። ባልንጀሮቼ ሲጎዱ ሳይ እኔም እጎዳለሁ፡፡ በቻልኩት ማህበራዊ ሚዲያዎቼን በተለያዩ ጠንካራ ይለፍቃሎች በመቆለፍ ስልኬንም እንዲሁ በማድረግ፣ በተጨማሪም ከሰዎች ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት ባለመቸኮል፤ እንደአስፈላጊነቱ አንዳንዶቹን በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ፣ አንዳንዶቹን ምናልባት በሰልክም ጭምር፣ አንዳንዶቹን ደግሞ በኣካል፣ በጣም ጥቂቶቹ ደሞ እስከ ቤተሰብ ድረስ አቀርባቸዋለሁ። ምክንያቱም ሁላችንም በዜግነታችን ምክንያት የተገፋን ብንሆንም የተለያየን ሰዎች ስለሆነን የትኛዉ ግንኙነት መርዛማ ሆኖ እንደሚጎዳን ስለማናውቅ መጠንቀቅ ግድ ነዉ።

 

 

በDating ዙሪያ ያለኝ ልምድ በጣም አነስተኛ ነዉ። ገና ዴቲንግ አፕ እንደጀመርኩ፤ አንደኔ የህይወት ዘመን የፍቅር ግንኙነት መመስረት የሚፈልግ ሰዉ ቶሎ የማገኝ እና የምገላገል ነበር የመሰለኝ። ከጥቂት ሰዎች ጋር የማዉራት እድል አግቻለሁ። ከኣንዱ ጋር ብቻ አንድ ቀን በኣካል ተገናኝተናል ነገር ግን ሊያስቀጥለን የሚችል መግባባት ላይ አልደረስንም። አሁንም ግን ፍለጋዬን አላቋረጥኩም። ያዉ dating app አንዱ እንጂ ብቸኛዉ የትዳር ጓደኛ ማግኛ መንገድ አይደለም። እግዚአብሔር እንዲረዳኝ እየጸለይኩ ነዉ፤ የሚሳካልኘም ይመስለኛል።

 

አንድ ቀን አንድ ለኣንድ የተወሰነ፣ ኣላማ እና እሴት ያለዉ፣ ለእኛ ለጥንዶቹ እንዲሁም ለማህበረሰባችን ነጻነት እና ደህንነት የበኩሉን የሚያደርግ፣ ማህበራዊ ሃላፊነቱን የማይረሳ፣ ለታናናሾቻችን ምሳሌ የሚሆን ጠንካራና መልካም ትዳር በሁለት ወንዶች መሀል የመሰረተ፣ ምሳሌ የሚሆን ትዳር ይኖረኛል ብዬ አምናለሁ። ይሔን ስል መልካም ትዳር በሁለት ወንዶች መሀል የመሰረተ፣ ምሳሌ የሚሆን ትዳር ይኖረኛል ብዬ አምናለሁ። ይሔን ስል ፍጹም የሆነ ነገር እየጠበቅኩኝ አይደለም፤ ነገር ግን በሒደት ወደማልመዉ አይነት ቅርጽ እና ማንነት የሚያድግ ዘር እየዘራሁ እያለፍኩ ስለሆነ ነው። ከእኔ የሚጠበቀዉ ያንን ትንሽ ዘር ማሳደግ እና ትልቁን እና ሙሉዉን ቅርጽ አየገነቡ መሔድ ነዉ። ዉጣ ዉረድ አለዉ? በደንብ! ዋጋ ያስከፍላል? አዎን! ግን ደግሞ ለ ፍቅር ግንኙነቱ ይገባዋል ብዬ የማምነዉ አይነት ተስፋ ካለኝ የምታገል ይመስለኛል። እግዚአብሄር ስለሚያሳካው ሰርጌን ካሁኑ ጠርቻችኋለሁ። 

 

 

በዚህ ሁሉ መንገድ ዉሰጥ የረዳኝን እግዚአብሔርን ደጋግሜ በልጁ በኢየሱስ ስም አመሰግነዋለሁ!!! ባለፉት አመታት ውስጥ ያገኘኋቸዉ የእድሜ ልክ ጓደኞቼ ናቸዉ ብዬ የማምነዉን ስማቸውን ለጥንቃቄ ሲባል መዘርዘር አስፈላጊ ባይሆንም ለመልካም ተጽዕኖኣቸዉ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ። እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካቸውም ዘንድ ምኞቴ ነው።

 

 

እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ለዘላለም ይኑር።

 

Published
Categorized as Amharic

Leave a Reply

Discover more from Yezare Abebawoch

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading